(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 18፣ 2014 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ "እንደ ሀገር በብዙ ተግዳሮቶች ሆነን፤ ፓርላማው ውጤታማ ሥራ አከናውኗል" ሲሉ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ ገለጹ፡፡

አፈ-ጉባዔው ይህንን የገለጹት፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተባባሪ ኮሚቴ፤ የምክር ቤቱን ቋሚ ኮሚቴዎች የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

ሀገሪቱ ችግር ውስጥ በምትገኝበት በዚህ ወቅት፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕግ አወጣጥ፣ በክትትል እና ቁጥጥር፣ በሕዝብ ውክልና እንዲሁም በፓርላማ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ እንደሆነ አፈ-ጉባዔው አስገንዝበዋል፡፡ ምክር ቤቱ ይህንን ስኬት ያገኘው፤ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው ሕዝብ እና መንግስት የጣሉባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ባሳዩት ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት እንደሆነም የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ታገሠ አስረድተዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ታገሠ፤ የሰላም እና ፀጥታ ሁኔታ፣ የኑሮ ውድነት ጉዳዮች፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የአግልግሎት ሰጪ ተቋማትን እንዲሁም የልማት ፕሮጄክቶችን የግንባታ አፈጻጸም መከታተል እና መቆጣጠር፤ የቋሚ ኮሚቴዎች ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፤ ፓርላማው የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር፣ የበኩሉን ድርሻ በብቃት መወጣት እንዳለበት አስምረው ተናግረዋል።

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፤ በብዙ ችግር ውስጥ ሆነን ኢትዮጵያን ለማሻገር የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ተግባር እንደሆነ እና ምክር ቤቱም በብዙ መልኩ ሀገሪቷን እያነቃቃ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴዎች የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ ሀገርን የሚያሻግር ብቻ ሳይሆን፤ ሌብነትን እና ብልሹ አሠራርን፣ በስልጣን አለአግባብ መጠቀምን እና የፍትሕ መዛባትን በማስቀረት፤ ዜጎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚያስችልም አስረድተዋል፡፡

የፓርላማውን መረጃዎች በወቅቱ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር በሚዲያ በኩል መሻሻሎች እየታዩ መሆናቸውንም ዋና ተጠሪው ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ፀሐፊ ዶክተር ምሥራቅ መኮንን የቋሚ ኮሚቴዎችን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፤ በምክር ቤቱ የዝግጅት ምዕራፍ፣ 11 ቋሚ ኮሚቴዎች እና 27 ንዑሳን ኮሚቴዎች መደራጀታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በተግባር ምዕራፍ ደግሞ፤ ቋሚ ኮሚቴዎች ዕቅድ አዘጋጅተው፣ ከአስፈጻሚ ተቋማት ጋር የጋራ ግንዛቤ ይዘው ወደ ሥራ እንደገቡ የገለጹት የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለሕዝብ እና ለሀገር የሚጠቅሙ ዘጠኝ አዋጆችን ምክር ቤቱ ማጽደቁን ገልጸዋል፡፡

ሌሎች አዋጆችም ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ለተጨማሪ ዕይታ እንደተመሩ እና በምክር ቤቱ እንዲጸድቁ የሚፈለጉ የወንጀል ምርመራ ማስረጃ እና የትራንስፖርት ረቂቅ ሕጎች መኖራቸውን፤ ዶክተር ምሥራቅ ጠቁመዋል፡፡

በሕዝብ ውክልና ሥራው ደግሞ፤ ቋሚ ኮሚቴዎች እስከታችኛው ማኅብረሰብ ወርደው ችግሮችን ማስተዋላቸውን እና የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያዝ መረጃ መሰብሰብ መቻላቸውን ዋና ፀሐፊዋ ተናግረዋል። በሌላ በኩል፤ የፓርላማ ዲፕሎማሲን በተመለከተ በትላልቅ ዓለም-አቀፋዊ ስብሰባዎች ኢትዮጵያ ስለ ሰላም ያላትን የፀና አቋም በሕዝብ ተወካዮች አማካኝነት እንዳንጸባረቀችም በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡

የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕ እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ እፀገነት መንግስቱ፤ የአዋጅ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ከተጠሪ ተቋማት ለኮሚቴው በርካታ ሰነዶች እየቀረቡ ስለሆነ፣ ምክር ቤቱ የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

የምክር ቤቱ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች፤ በሪፖርቱ መሠረት በርካታ ሐሳቦችን፣ አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን አቅርበዋል። በዚህም የተነሳ ሰፋፊ ውይይቶች ከተካሄዱ በኋላ፤ በተከበሩ አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ቀጣይ አቅጣጫዎች ተመላክተው፤ ስብሰባው ተጠናቅቋል።

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ