(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 28፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ፤ "በብዙ ውጣ-ውረድ ታጅበንም ቢሆን ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል" ሲሉ የምክር ቤቱን የአፈጻጸም ደረጃ አመላከቱ፡፡

አፈ-ጉባዔው ይህንን ያመላከቱት፤ የምክር ቤቱ አማካሪ እና አስተባባሪ ኮሚቴዎች እንዲሁም የመንግስት ዋና እና ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታዎች በተገኙበት፣ የ11ዱም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ሲገመገም በሰጡት አስተያየት ነው፡፡

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ፤ ከንመግስት ምስረታው ጊዜ ጀምሮ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ፣ ምክር ቤቱ ለሀገር ግንባታ ትልቅ አስተዋጽዖ ማበርከቱን አንስተዋል፡፡

እንደ ሀገር እና እንደ ተቋም የተሠሩ ሥራዎች አበረታች እንደሆኑ እና በቋሚ ኮሚቴዎች የቀረቡት ተጨማሪ ሐሳቦች አስተማሪ ሊሆኑ እንደሚችሉም አመላክተዋል። ስለሆነም ቆም ብለን በማሰብ፣ ሀገራችንን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ፣ የሁላችንም ቀና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴዎች የተቋማት የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎቻቸው በውጤት የታጀቡ፣ የሕዝቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

በጋራ፣ በትብብር እና በቡድን ተቀናጅቶ በመሥራት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያስረዱት አፈ-ጉባዔው፤ የውክልና ሥራን በአግባቡ ለመወጣት፣ ከሕዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን መፍታት እና በየደረጃው ካሉ አመራር ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ታገሠ አክለውም፤ የተቋማት ዕቅዶች ከሀገሪቷ የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታ ጋር መዛመዱን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች፤ ከሂደት ይልቅ ውጤትን መሠረት ያደረገ ክትትል እና ግምገማ በማድረግ፣ ተጠያቂነትን እንዴት እናስፍን በሚሉ ጉዳዮች ላይ አጽንዖት ሰጥተው እንዲሠሩም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ፤ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚከታተሏቸው ተቋማት እያንዳንዳቸው ዕቅዶቻቸውን ፈጥነው እንዲልኩላቸው ማድረግ እንዳለባቸውም፣ አያይዘው አሳስበዋል፡፡

የተከበሩ ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፤ የምክር ቤቱ ግርማ ሞገስ በሥራ የሚገልጽ መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም፤ ጥሩ የሠሩ ተቋማት የሚበረታቱበት፣ ያልሠሩት ደግሞ የሚጠየቁበት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ይገባል ብለዋል፡፡

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፤ በምክር ቤቱ መሻሻሎች እንዳሉ አንስተው፣ የምክር ቤቱ አባላት ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የክትትል እና ቁጥጥር ሥራቸውን ምክር ቤቱን በሚመጥን ደረጃ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴዎች አባላት፤ እንደ ገቢዎች፣ ንግድ፣ ትራንስፖርት እና ከተማ-ልማት ባሉ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲሁም ለፕሮጄክቶች አፈጻጸም ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴዎች በቀጣይ ትኩረት በሚፈልጉ ምጣኔ-ሀብታዊ ዘርፎች ማለትም በአምስቱ የኢኮኖሚ የዕድገት ምንጮች በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT)፤ ማዕድን እና ቱሪዝም ተመሥርተው የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎቻቸውን ማከናወን እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴዎች አመራሮች እና አባላት በሕዝቦች ዘንድ በሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፣ በሙስና፣ በብልሹ አሠራሮች ላይ ግልጸኝነትን እና ተጠያዊነትን እያረጋገጡ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

በፍትሕ ተቋማት፣ በኑሮ ውድነት እና በዋጋ ግሽበት ረገድ ከሕዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መልኩ መሥራት ካልተቻለ፤ እንደ ሀገር ትልቅ ውድቀትን ሊያስከትል እንደሚችልም አስገንዝበዋል፡፡

ከግብርና አንጻርም መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በግብርና ሜካናይዜሸን የኩታ-ገጠም እርሻዎችን በማስፋት፤ የበጋ ስንዴን ምርታማነት በመስኖ በማሳደግ፣ ዜጎች ራሳቸውን ከምግብ ጥገኝነት እንዲያወጡ ለማድረግ እና ሀገራችን ስንዴን ወደ ውጭ እንድትልክ ጭምር በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ለሀገራችን ውድቀት ዋናው መንስዔ የትምህርት ሥርዓት ውድቀት በመሆኑ፤ የምክር ቤቱ አባላት የትውልድ ግንባታን አልመው የተቋማትን የትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርኃ-ግብሮችን ዓቅም ማጎልበት እንዳለባቸው፣ ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የተከበሩ ረዳት ፕሮፌሰር ምሕረቱ ሻንቆ በኩላቸው፤ የምክር ቤቱ ዋና ተግባር በሕገ-መንግስቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት መወጣት መሆኑን ጠቁመዋል። ሂደትን ሳይሆን ውጤትን መሠረት በማድረግ፤ በክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎች የተገኙትን ውጤቶች አንድ ሁለት ብሎ በሪፖርቱ ማስቀመጥ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ አክለውም፤ ቋሚ ኮሚቴዎች ግብረ-መልስ ሲሰጡ በአምስት ዓመቱ መሪ ዕቅድ ውስጥ ማሻሻል እና ማረጋገጥ በሚል በተቀመጠው ግብ መሠረት ተሰርቷል፣ አልተሰራም የሚለውን ማረጋገጥ (Check and balance) ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የ11ዱም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፤ በክትትል እና ቁጥጥር፣ በሕግ-አወጣጥ፣ በፓርላማ ዲፕሎማሲ እና በሕዝብ ውክልና ሥራዎች ምክር ቤቱ በተሰጠው ስልጣን እና ኃላፊነት መሠረት፤ የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጻም ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡

በመሠረተ-ልማቶች፣ በሕንጻ ግንባታዎች፣ በዜጎች ፍትሐዊ የቤት ተጠቃሚነት፣ በትራንስፖርት፤ በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች፤ እያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ በሚከታተላቸው ተቋማት በውጤት የተመሠረቱ ሥራዎችን በመሥራት፤ የሕዝብን ጥያቄዎች መመለስ እንዳለበትም የምክር ቤቱ አማካሪ ኮሚቴ አባላት አስገንዝበዋል፡፡

በ መኩሪያ ፈንታ