"በኦዲት ግኝት ለውጥ ያላሳዩ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል" አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
"በኦዲት ግኝት ለውጥ ያላሳዩ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል" --- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
(ዜና ፓርላማ) ሰኔ 17፣ 2017 ዓ.ም፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት በሚታይባቸው ተቋማት ላይ የምክር ቤቱን አሰራር ተከትሎ በቀጣዩ 2018 ዓ.ም ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ በተካሄደው የምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 39ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርትን አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት ተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት የሚታይባቸውና እርምት የማይወስዱ ተቋማትን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር መኖሩን ጠቁመው፤ በቀጣዩ 2018 በጀት ዓመት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች እና ባለድርሻ አካላት የአሰራር ሂደቱን ጠብቆ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል እቅድ አውጥቶ መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስተባባሪነት ሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች በእቅዳተው ውስጥ አስገብተው በተቋማት ያለውን የኦዲት ግኝት መገምገም እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በቋሚ ኮሚቴዎቹ እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት የተደረገውን አጠቃላይ ግምገማ መነሻ በማድረግ የኦዲት እርምት በማያደርጉ ተቋማት ላይ ህጋዊ፣ ፓለቲካዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አፈ ጉባኤው ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ለምክር ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት ተቋማት መመሪያን ሳይከተሉ ከ404 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ግዢ መፈፀማቸውን ገልጿል፡፡
ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ባቀረቡት ሪፖርት፤ በ70 የፌዴራል ተቋማት እና በ7 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቻቸው ከ404 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥትን የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ግዢ ተፈጽሞ ተገኝቷል ብለዋል።
መመሪያን ሳይከተሉ ግዢ ከፈፀሙ ተቋማት መካከል የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እንደሚገኙበት ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ተናግረዋል፡፡
አንዲሁም አርሲ ዩኒቨርሲቲ እና በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር-2 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከእነዚህ ተቋማት መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives