(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 4፣ 2014 ዓ.ም.፤ ቢሾፍቱ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ፤ "የዴሞክራሲ ተቋማት በዚህ ፈታኝ ወቅት ሀገሪቱን እየፈተኑ ያሉ ፈተናዎችን ለመሻገር፣ በጋራ መቆም ይገባል" ሲሉ ሐሳባቸውን ገለጹ።

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ይህንን የገለጹት፤ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘውን ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማትን ዓመታዊ የምክክር መድረክ በይፋ በከፈቱበት ንግግራቸው ነው።

እነዚሁ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የተከበሩ አፈ-ጉባዔ እንደተናገሩት፤ ሥራቸውን የበለጠ በማጠናከር፣ ዘላቂ እና ዘመን ተሻጋሪ ተቋም በመገንባት፤ በአሁኑ ጊዜ የሚስተዋሉትን ሀገራዊ ተግዳሮቶች ለመፍታት መተባበር ይገባቸዋል።

አክለውም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚስተዋሉ ችግሮች በመውጣት፤ ለዜጎች የተመቸች ሀገር ለመፍጠር፣ እኛ ኢትዮጵያዊን በዚህ ፈታኝ ወቅት በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡

"ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ከኢትዮጵያዊን ባሕል እና ዕምነት ያፈነገጡ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች በዜጎች ላይ ሲፈጸሙ ይስተዋላል። ከነዚህ እና መሰል ፈተናዎች ለመሻገር በመቀራረብ፣ በጋራ ልንሠራ ይገባል" የተከበሩ አፈ ጉባዔ ለመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክታቸው እንዳመለከቱት።

ከምንም ከማንም በላይ የዜጎች ሰላም እና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊጠበቅ ይገባል ሲሉም በአጽንዖት አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህም ሲባል የዴሞክራሲ ተቋማት ሥራቸው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን፤ የሕግ ማሻሻያ፣ የሰው ኃይል ግንባታ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራርን በመከተል፣ ሥራዎችን ማዘመን እንደሚገባቸው የተከበሩ አፈ-ጉባዔ አስገንዝበዋል፡፡

ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት ከምክር ቤቱ ጋር በሚያካሂዱት ዓመታዊ የምክክር መድረካቸው፤ በበጀት ዓመቱ የዕቅድ አፈጻጸም የነበሯቸውን ስኬቶች እና ተግዳሮቶች አንስተው ይወያዩበታል።

እንደዚሁም እያንዳንዱ የዴሞክራሲ ተቋም ከምክር ቤቱ የሚፈልገውን ድጋፍ ለይቶ የሚያቀርብ ሲሆን፤ በተመሳሳይም ምክር ቤቱ ከእነርሱ የሚጠብቃቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ተነጋግረው የጋራ መግባባት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ፤ ከምክር ቤቱ ጋር ከሚያደርጉት ግንኙነት ባሻገር ርስ በርሳቸው የተጠናከረ ግንኙነት በሚመሠርቱበት ሁኔታም እንደሚመካከሩ መረዳት ተችሏል።

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ