(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 8፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ፤ "ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ፤ ከለውጡ ወዲህ ትኩረት የተሰጠው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የላቀ ድርሻ አለው" ሲሉ የዘርፉን ጠቀሜታ ገለጹ፡፡

አፈ-ጉባዔው ይህንን የገለጹት፤ "አሻራችንን ለትውልዳችን፤ ለትውልድ እንሥራ፤ ለኢትዮጵያ እንትከል!" በሚል መሪ ቃል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በዛሬው ዕለት በየካ ሚሌኒየም ፓርክ የችግኝ ተከላ መርኃ-ግብር ባካሄዱበት ወቅት ነው፡፡

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ አያይዘውም፤ አረንጓዴ አሻራ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ፣ ለቀጣይ ትውልድ ተስፋ ለመጣል እንዲሁም የተጀመረውን ብልጽግና በሚፈለገው መልኩ ለማሳካት ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ይህ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ፣ አፈር እንዳይሸረሸር እና ለምነቱ እንዲጠበቅ እንዲሁም የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለማሳደግ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚረዳ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አስረድተዋል፡፡

የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ዐበይት ጉዳዮች መካከል አረንጓዴ አሻራ አንዱ አቅጣጫ በመሆኑ፤ ሕዝቡ የበኩሉን አስተዋጽዖ ሊያበረክት እንደሚገባም አፈ-ጉባዔው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የማስቀመጥ ሥራ የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ እንደ መንግስት ታምኖበት በከፍተኛ ንቅናቄ ወደ ሥራ ተገብቶ፤ ባለፉት አራት አመታት አበረታች ለውጦች እንደታዩበትም ገልጸዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ በአጭር እና በረጅም ጊዜ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የገለጹት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያም፣ አፍሪካም ብሎም የተቀሩት የዓለም ሀገራት ከገጠሟቸው ውስብስብ ተግዳሮቶች ለመውጣት ፍቱን መድኃኒት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የምር ቤት አባላት በዚህ ክረምት ወቅት ወደ ተመረጡባቸው አካባቢዎች ሲሄዱ ትኩረት ከሚሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል የአረንጓዴ አሻራ ማስቀመጥ፣ የግብርና ሥራውን ማጠናከር እና ሀገሪቷን እየገጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመፍታት መሥራት እንደሚገኙባቸው የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ አስገንዝበዋል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ከ18 ቢሊዮን በላይ ከተተከሉት ችግኞች መካከል 85 በመቶ መጽደቃቸውን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ ሕዝቡ በአረንጓዴ አሻራው መርኃ-ግብር የላቀ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ እና የተተከሉ ችግኞችንም መንከባከብ እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል፡፡

የምክር ቤት አባላትም በአረንጓዴው አሻራ መርኃ-ግብር ንቅናቄ በመፍጠር፤ መራጭ ሕዝባቸውን በማሳተፍ፣ በዚህ ክረምት የተሻለ ሥራ እንደሚያከናውኑም ተናግረዋል፡፡