(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 12፣ 2014፤ አዲስ አበባ፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ የቀጣዮቹን ሦስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ እና የ2015 ዓመታዊ የተግባር ዕቅድ፣ ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ አመራር አቀረበ።

በዛሬው ዕለት በቀረበው በዚህ የዕቅድ ምዕራፎች ገለጻ፤ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን ኣርአያ እና ሌሎች የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።

ኮሚሽኑ ባለፉት አራት ወራት ያከናወናቸውን ዐበይት ሥራዎች ለምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ያቀረበ ሲሆን፤ ለ2015 በጀት ዓመት የሚያስፈልገውን በጀትም ከዕቅዱ ጋር አያይዞ አሳውቋል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ በዚህን ወቅት፤ "እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሚናውን በአግባቡ ሲወጣ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ይሆናል" በማለት፣ የዜጎችን ያልተቆጠበ ተሳትፎ አስፈላጊነት አስገንዝበዋል፡፡

የኮሚሽኑ ረቂቅ ስትራቴጂክ ዕቅድ እና የ2015 ዓ.ም. የድርጊት መርኃ-ግብር ቀርቦ ከምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት በተደረገበት ወቅት፤ የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ይህንን ማስገንዘቢያ ሰጥተዋል፡፡

ለሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንዲሁም የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ምሁራን፣ መንግስታዊ አካላት እና የተለያዩ የሙያ ማኅበራት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ከተወጡ፤ የታለመውን ሀገራዊ መግባባት ዕውን ማድረግ እንደሚቻል የተከበሩ አቶ ታገሠ አስረድተዋል፡፡

ሕዝቡ በመረጠው አጀንዳ ላይ በነጻነት ተወያይቶ የሚያቀርበውን ውሳኔ በክብር ለመቀበል መንግስትም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው፤ የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አሳስበዋል፡፡

ምክትል አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፤ በየማኅበረሰቡ ያሉትን ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ተቋማት መጠቀም ቢቻል፣ አጠቃላይ ሕብረተሰቡ እየተደማመጠ እና እየተማመነ ተወያይቶ ወደ መግባባት መድረስ እንደሚችል ለኮሚሽነሮቹ ባቀረቡት ምክረ-ሐሳብ አብራርተዋል፡፡

የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የዚህ ኮሚሽን ዋነኛ ተልዕኮ እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላም መገንባት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ስኬታማ ይሆን ዘንድም የመንግስት ቁርጠኛ አቋም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አጀንዳ በማመንጨት ሂደቱም ማኅበረሰቡን ጨምሮ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና የተለያዩ የሙያ ማኅበራት ተሳታፊ እንዲሆኑ ቢደረግ፤ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

በምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ተጨማሪ አስተያየትና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፤ በኮሚሽኑ ሰብሳቢ በፕሮፌሰር መስፍን ኣርአያ እና በሌሎች ኮሚሽነሮች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በ አበባው ዮሴፍ