(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 18፣ 2014፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ፤ “ከሀገራዊ ምክክሩ ሀገር የሚያሻግር ሐሳብ ይጠበቃል” ሲሉ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናገሩ።

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፤ በቅርቡ በሚጀመረው ሀገራዊ የምክክር መድረክ የሚሳተፉ አካላት በሙሉ ከግጭት አዙሪት የሚያወጣን እና ሀገራችንን የሚያሻግር ሐሳብ እንዲያቀርቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የአካባቢውን ባሕል እና ወግ ተጠቅሞ እንደ ሀገር መግባባት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር ለመስማማት መሞከር፤ መስማማት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማስቀመጥ ከሀገራዊ ምክክሩ እንደሚጠበቅ፣ አፈ-ጉባዔው አስረድተዋል::

ሕብረተሰቡ በታሪክ፣ በሕገ-መንግስታዊ ጉዳዮች እንዲሁም በሌላ በመረጠው አጀንዳ ላይ ነጻ ሆኖ የሚወያይባቸው መድረኮች እንደሚዘጋጁም የተከበሩ አቶ ታገሠ ጠቁመዋል።

የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማ ቀደም ሲል የተፈጸሙ ስህተቶች እንዳይደገሙ፤ የነበሩት መልካም ተሞክሮዎች ደግሞ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል እንደሆነም አፈ-ጉባዔው አስገንዝበዋል።

ሕዝቡ ተወያይቶ የሚያቀርባቸውን ውሳኔዎች በክብር ለመቀበል እና ተግባራዊ ለማድረግ መንግስትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው፤ የተከበሩ አፈ-ጉባዔ አክለው አሳስበዋል።

በ አበባው ዮሴፍ