(ዜና ፓርላማ)፤ ነሐሴ 02፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)፤ “የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ተልዕኮውን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል” ሲሉ አሳሰቡ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ማሳሰቢያውን የሰጡት፤ ከኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በኮሚሽኑ የ2015 የበጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ በዛሬው ዕለት ውይይት በተካሄደበት ወቅት በሰጡት ሐሳብ ነው፡፡

ሰብሳቢው የተከበሩ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) በሀገራችን በየቦታው በተፈጥሮ እና በሰው-ሠራሽ ችግሮች የተፈናቀሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል ኮሚሽኑ የአደጋ ስጋት ተደራሽነትን ማስፋት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የአደጋ ቅልበሳውን በአግባቡ ለመወጣትም፤ በዕቅድ መንቀሳቀስ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ሰብሳቢው አክለውም፤ እየተከሰተ ባለው የዝናብ ዕጥረት መንስዔ በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ፈጥኖ ለመድረስ፤ የኮሚሽኑ ቅድመ-ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑን አበክረው አንስተዋል፡፡

ተቋሙ ተልዕኮውን በአግባቡ ለመወጣት በሙያተኛ እና በአደረጃጀት ብቁ ሆኖ መገኘት እንዲሁም ከክልሎች እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት ግልጽ መሆን እንዳለበት እና የተጠያቂነት አሠራር ሥርዓት ማስፈን እንደሚገባው ሰብሳቢው አሳስበዋል፡፡

የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ፈቲሂ ማህዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኮሚሽኑ አመራሮች ማብራሪያ እና ምላሽ በሚሹ ጉዳዮች ፈጥነው ምላሽ መስጠት አለባቸው ብለዋል፡፡ ሙስና መከላከል የመጭው ዓመት ተቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሃይድሩ ሃሰን በበኩላቸው፤ በሀገራችን ከ15 ሚሊዮን 4 መቶ በላይ በተፈጥሮ እና በሰው-ሠራሽ አደጋ የተፈናቀሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን አስታውሰዋል፡፡ በዝናብ ዕጥረት የሚከሰተውን አደጋ ለመቀልበስም በዕቅድ እየተሠራ መሆኑን አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም ከቋሚ ኮሚቴው የተነሱ ሐሳቦች ገንቢ እና አስተማሪ በመሆናቸው፤ በግብዓትነት በመጠቀም በዕቅድ አካትተው በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

ሌሎች የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ደግሞ በጎርፍ፣ በግጭት፣ በድርቅ እና በተመሳሳይ ዘርፈ-ብዙ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ ቢሆንም፤ ለአሠራር ማነቆ የሆኑ የፋይናንስ መመሪያዎችን፣ ደንቦችን እና ፖሊሲዎችን ለማሻሻል ቋሚ ኮሚቴው የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- መኩሪያ ፈንታ

ቀን፡- ነሐሴ 02፣ 2014 ዓ.ም