(ዜና ፓርላማ)፤ መስከረም 9፣ 2015 ዓ.ም.፤ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ በመሆን “ደማችን ለመከላከያ ሰራዊታችን” በሚል መሪ ቃል የደም ልገሳ መርሃ-ግብር አከናውነዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት እንዲሁም የሁለቱ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ አመራሮች እና ሰራተኞች ተገኝተው ደም ለግሰዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ የሀገራችንን ሉአላዊነት ለማስከበር በየትኛውም መስክ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን ይኖርብናል በማለት ገልጸው ደም መለገሳቸውን ተከትሎ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በልጆችዋ መስዋዕትነት ታፍራ እና ተከብራ የምትቀጥል ሀገር እንደመሆኗ ይሄ መርሃ-ግብር የዚህ ታሪክ አካል ነው ብለዋል፡፡

አክለውም እኛ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ስንቆም እና ስንተባበር ሀገራችንን ልናሻግር እንደምንችል አስታውሰው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እና በዚህ ጦርነት ለተጎዱ ወገኖቻችን ደም በመለገስ ህይወትን መታደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

አፈ-ጉባዔው አያይዘውም በዚህ ጦርነት የሀገራችንን ሉአላዊነት ለማስከበር ብዙ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ወገኖቻችንን በየተሰማራንበት ሁሉ የሚጠበቅብንን ማበርከት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው ሀገር ነጻነትዋ ሲደፈር ጠላት ሀገርን ለመበተን ከውጭም ከውስጥም ሲዘምት የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን የዜጎችን ነጻነት እና ክብር ለማስከበርና ውድ ዋጋ ለሚከፍል ጀግና ደሜን ስለግስ ታላቅ ደስታ እየተሰማኝ ነው ብለዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ዘሃራ ኡመድ እንዳሉትም መከላከያ ሰራዊታችን በጫካ እየተዋደቀ ያለው የኛን ሰላም ለማስከበር እና ሁላችንም በተሰማራንበት የስራ መስክ ውጤታማ እንድንሆን እንዲሁም በሰላም ወጥተን እንድንገባ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ቀላል ባለመሆኑ በደም መፍሰስ ምክንያት ህይወታቸውን እንዳያጡ መደገፍ እና እያበረከቱ ስላሉት አስተዋጽኦ ማመስገን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ዶ/ር ምስራቅ መኮንን በበኩላቸው የመከላከያ ሰራዊታችን የሀገራችንን ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ ህይወቱን በሚሰጥበት እና አካሉን በሚያጣበት ሁኔታ ውስጥ ደም በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ይህ የደም ልገሳ ፕሮግራም ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡

በ ለምለም ብዙነህ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ