"የመሀል ዘመን ዕድልን" በመሻገር ለውጤት መብቃት ይገባል”

       --- የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (/) ---

(ዜና ፓርላማ) ሚያዚያ 22 ቀን፣ 2017 .ም፤ አዲስ አበባ፤ "የመሀል ዘመን ዕድልን" በመሻገር ሀገራዊ ለውጡን ለውጤት ማብቃት ይገባል ሲሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (/) ገለጹ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት፤ ለምክር ቤት አባላት እና ለተቋማት የስራ ኃላፊዎች በሰጡት ስልጠና ነው፡፡

በአንድ ሀገር ስርዓታዊ ሽግግር ለውጥ ሂደት ውስጥ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በመሻገር ለውጤት ለመብቃት የአመራር ሚና ወሳኝ እንደሆነ ሚንስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹የመሀሉን ዘመን›› ሽግግር ከመነሻው ከፍ ያለ፤ ለከፍተኛ ውጤት ለመድረስ እና ግቡን ለማሳካት የተቋማት የአመራር ብቃትን የሚጠይቅ መሆኑን የተከበበሩ ተስፋዬ በልጅጌ( /) አመላክተዋል፡፡

ዓለም በብዝሃ ቀውስ ባለችበት ወቅት፤ኢትዮጵያ በውስጥ እና በውጭ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ተቋቁማ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው እምርታዊ ለውጦችን እያስመዘገበች ያለች ሀገር መሆኗንም ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ጠቅላላ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት 8.4 በመቶ እንደሚጠበቅ የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (/ ) ጠቁመዋል፡፡

መንግስት የህዝቡን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ ለመድኃኒት፣ ለማዳበሪያ፣ ሸቀጣ ሸቀጥ እና ለምግብ ዘይት 211 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማደረጉንም ገልጸዋል፡፡

በዘመናት የተገኘውን መልካም ዕድል ትውልዱ ተረድቶት ለጋራ የሀገር ጥቅም በአንድነት መቆም እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ህገ መንግስታዊ ስርዓትን ያከበረ በህዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያለው ነፃ እና ገለልተኛ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት መገንባት እንደሚገባም ሚኒስትሩ አያየዘው ጠቁመዋል፡፡

ከህገ መንግስት መሻሻልና ከወል ትርክቶች ጋር በተያያዘ በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እልባት የሚያገኙ መሆናቸውን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ከቀይ ባህር ጋር በተያያዘ የሀገርን ነበራዊና ታሪካዊ ዳራን ያገናዘበ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ታሳቢ ያደረገ ሰጥቶ በመቀበል መርህ የሚፈፀም መሆኑን የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (/) አስረድተዋል፡፡

ከሰላም እና ፀጥታ ጋር በተያያዘ እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶችን መንግስት በዘላቂነት መፍታት እንዳለበት የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡

ከኑሮ ውድነቱ እና ከዋጋ ግሽፈቱ ጋር በተያያዘ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታዎች አሁንም እየተነሱ በመሆናቸው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አንደሚገባ የምክር ቤት አባላት አስገንዝበዋል፡፡

ለሀገር ግንባት ተቋማት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንዳለባቸው እና በመርህ ላይ የተመሰረተ ትውልድ ለመፍጠር ህዝቡ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡

(በመኩሪያ ፈንታ)