"የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በህዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚፈታ ነው"
"የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በህዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚፈታ ነው"
----- የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ----
(ዜና ፓርላማ) ሚያዝያ 20 ቀን ፣2017 ዓ.ም.፤ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በህዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚፈታ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እና ምክትል አፈ-ጉባኤ፣ የምክር ቤቱ አማካሪና አስተባባሪ ኮሚቴ እና የጽህፈት ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመገኘት የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
በጉብኝቱም ለምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ወ/ሮ አለምፀሐይ ጳውሎስ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ስለ ማዕከሉ አገልግሎት አሰጣጥ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።
በገለፃውም በማዕከሉ በ12 ተቋማት 41 የሚደርሱ አገልግሎቶች እንደሚሰጡም ተብራርቷል።
የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በአንድ ማዕከሉ በቅብብሎሽና በቅንጅት አገልግልት የሚሰጡ የተለያዩ ተቋማትን የስራ እንቅስቃሴንም ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በጉብኝቱ ማብቂያም የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ምክር ቤቱ በሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የህዝብ ውክልና ስራ ከህዝብ ከሚነሱት ቅሬታዎችና ጥያቄዎች መካከል በየተቋማቱ የሚሰጡ አገልግሎት አና የመልካም አስተዳደር ችግር ዋናው ነው ብለዋል።
ስለሆነም በመንግስት የሚሰጡ አገልግሎቶች፣ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ወጪ ቆጣቢ እና የህዝብን ቅሬታ፣ ምልልስና ድካም የሚቀንሱ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ይህ ተቋም የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈታ ነው ያሉት የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ የማዕከሉ አገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊ፣ የተገልጋዮችን ቅሬታ የሚፈታ እንዲሁም ወጪን፣ ጊዜና እና ጉልበትን የሚቀንስ መሆኑንም አብራርተዋል።
ማዕከሉ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ዘመናዊ፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን የሚያስቀር፣ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከህዝብ የሚነሳውን ቅሬታና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታ በመሆኑ ምክር ቤቱ በጉብኝቱ መደሰቱን ተናግረዋል።
የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ይህን መሰል ለሀገር ትልቅ አስተዋፅኦ የሚሰጥ ተቋምን በመገንባት ረገድ የበኩላቸው ጥረት ያደረጉ አካላት ሊመሰገኑ እንደሚገባ እና ተቋማቱን በመደገፍና በማጠናከሩ ረገድም ሁሉም አካል የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
ምክር ቤቱም ማዕከሉን በህግ ማዕቀፍ፣ በክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በህዝብ ውክልና ስራው አካቶ በመስራት እንደሚደግፍም ነው ያስገነዘቡት።
(በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ)
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives