(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 07፣ 2014 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳሰቡ፡፡

ምክር ቤቱ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ከአስፈጻሚ አካላት ጋር በተወያየበት ወቅት ነው ማሳሰቢያው የተሰጠው፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በየተመረጡበት አካባቢ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን በተለይ የመጠጥ ውኃ እና የመስኖ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ ነው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር የተወያዩት፡፡

የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ለመከታተል የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም በፌዴራል እና በክልል ደረጃ የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን በመለየት በየመዋቅሩ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ የተከበሩ አቶ ታገሠ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በጣም የቆዩ እና ብዙ ቅሬታ ላለባቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ በመስጠት ውዝፍ ችግሮችን ለመፍታት ከክልሎች ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አፈ-ጉባዔው ተናግረዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ሚንስትር ኢንጂነር አይሻ መሐሙድ በምክር ቤት አባላት አማካኝነት ከህብረተሰቡ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ የተጋነነ የካሳ ጥያቄ፣ የጸጥታ ችግር እና ብልሹ አሰራር ለፕሮጀክቶቹ መጓተት ማነቆ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በዘንድሮው ዓመት ለ5.2 ሚሊዮን ህዝብ የንጹ መጠጥ ውኃ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፤ ለፕሮጀክቶች የሚያዘው ዋጋ እና ጨረታ ሲወጣ የሚጠየቀው ገንዘብ የማይጣጣሙ በመሆናቸው አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ለመጨረስ እንዳስቸገረ ገልጸዋል፡፡

በ አበባው ዮሴፍ