(ዜና ፓርላማ)፣ ሰኔ 29፣ 2015 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ ከመላው ኢትዮጵያ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት፤ ምክር ቤቱ ባካሄደው 28ኛ መደበኛ ስብሰባው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡት ወቅት ነው፡፡

ክቡር ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ መንግሥት በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ከቀያቸው ለመመለስ በትኩረት እየሰራ መሆኑንና አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ያስታወቁት፡፡

ባለፉት ዓመታት በበጎ አድራጊ ግለሰቦች ድጋፍ ከ60 ሺህ በላይ የአቅመ-ደካማ ቤቶችን በማፍረስና እንደገና በመገንባት ለነዋሪዎች መተላለፉን ገልፀው፤ 5 ሺህ ለኪራይ የሚውሉ ቁጠባ ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም አክለውም አብራርተዋል፡፡

ሕገ-ወጥ የቤት ግንባታዎችን ለመከላከል ሁሉም አካላት ተረባርበው ማስቆም ካልተቻለ ችግሩ የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስገንዝበው፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገነቡ ሕገ-ወጥ ግንባታዎችን ለማስቆም ከሁሉም የክልል አስተዳደሮች ጋር ስምምነት መድረሱን ዶክተር ዐቢይ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከ700 ሺህ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ እንዲመገቡ መደረጉን እና በአዲስ አበባ ከተማ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ የሚመገቡበት 17 የመመገቢያ ጣቢያዎች መኖራቸውን እና በዚህም ማዕድ ማጋራት ላይ ትልቅ ስራ መሰራቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በቀን 300 ሺህ ዳቦ ሲጋግር የነበረውን ፋብሪካ በማሻሻል በአሁኑ ወቅት ወደ 4 ሚሊዮን ዳቦ የሚጋግር ፋብሪካ መገንባቱን ዶክተር ዐቢይ ጠቁመው፤ በቀን 280 ሺህ እንጀራ የሚጋግር የእንጀራ ፋብሪካ መገንባቱንም አብራርተዋል፡፡

በመደመር መንገድ መጽሐፍ ሽያጭ በመላ ሀገሪቱ 30 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውንና ከሽያጩ 3 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ቅርሶችን ለማደስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በ ጋሹ ይግዛው

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡- 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR 
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ