(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 5፣ 2014 ዓ.ም.፤ ቢሾፍቱ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ፤ “የዴሞክራሲ ተቋማት ምክር ቤቱ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች አጋዥ ክንድ ሊሆኑ ይገባል” ሲሉ ሐሳባቸውን ገለጹ፡፡

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ይህንን የገለጹት፤ ለምክር ቤቱ ተጠሪ ከሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት ጋር ምክር ቤቱ ባካሄደው ዓመታዊ የጋራ ፎረም በሰጡት ሐሳብ ነው፡፡

ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት፤ ምክር ቤቱ በሚያከናውናቸው ተግባራት፣ በተለይም በክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎች ተገቢውን ለውጥ ለማምጣት በሚያደርገው ጥረት ዓይነተኛ አጋዥ መሣሪያ ሊሆኑ እንደሚገባ፤ አፈ-ጉባዔው አስረድተዋል፡፡

የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታን በዘላቂነት ማረጋገጥ ለሀገር ዕድገት እና ብልጽግና የማይተካ ሚና እንዳለው የገለጹት አፈ-ጉባዔው፤ እነዚህ ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ የሕዝብ አገልጋይ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አፈ-ጉባዔው፤ ምክር ቤቱ ከተጠሪ ተቋማት ጋር የጋራ ፎረም ያካሄደበት ዋናው ምክኒያት፤ የአሠራር ችግሮችን በትብብር ለመፍታት፣ ቅንጅታዊ አሠራሮችን የበለጠ ለማጠናከር እና የዴሞክራሲ ተቋማትን ችግሮች ለይቶ ድጋፍ ለማድረግ ነው ሲሉ የፎረሙን ዓላማ አስረድተዋል፡፡

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ፤ “የዴሞክራሲ ተቋማት ሀገር የማጽናት ዓቅም አላቸው፡፡ የእነዚህ ተቋማት ሥራዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ በቀጣይ አስፈላጊው የሕግ ማሻሻያ እና የተለያዩ ድጋፎችም ይደረጉላቸዋል” ብለዋል፡፡

የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፤ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑት የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ እንዲሆኑ የለውጡ መንግስት ዘርፈ-ብዙ ማስተካከያዎችን ማድረጉን አስታውሰው፤ መሻሻሎችንም እያሳዩ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡ ሀገሪቷም የዴሞክራሲ ሥርዓት ልምምድ እንደጀመረች ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መካሄዱን፤ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ ለአብነት አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል የዴሞክራሲ ተቋማት የበጀት፣ የመዋቅር እና ገለልተኛ እንዳይሆኑ የተለያዩ ተጽዕኖዎች እንዳሉባቸው ከውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡

እነዚህ የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ እንዲሁም ለሕዝብ የቆሙ እና ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ ከተፈለገ፤ በጀትን ጨምሮ ያሉባቸው ውስብስብ ችግሮች እንዲፈቱ እና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችም እንዲደረጉላቸው ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ክቡር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ደግሞ፤ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመከላከል እና የሰውን ሕይወት በግፍ የቀጠፉ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት ለአስፈጻሚው የመንግስት አካል ከማቅረብ ባለፈ፤ ተቋሙ ለተጎጂ ዜጎች ድምጽ ለመሆን ሁለንተናዊ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

የጥላቻ ንግግር እና የሐሰት መረጃ፣ የግጭት አዘጋገብ ዓቅም ማነስ፣ የመረጃ ዕጦት፣ የጎራ መደበላለቅ እና የሚዲያ ባለቤትነት ፈቃድ አሰጣጥ ችግሮች፤ በመገናኛ ብዙኃን የታዩ ትኩረት የሚሹ ዐበይት ነጥቦች መሆናቸውን ደግሞ፤ የኢትዮያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዳይሬክተር ጄኔራል ክቡር መሐመድ እድሪስ አስረድተዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉት የዴሞክራሲ ተቋማት፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ናቸው፡፡

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ