(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 18፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ “የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች 6ኛው ምክር ቤት በ2ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ፤ ለሰላም፣ ፀጥታ እና ደኅንነት ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል” ሲሉ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ አስገነዘቡ።

አፈ-ጉባዔው ይህንን ያስገነዘቡት፤ በዛሬው ዕለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ በማውጣት፣ በክትትል እና ቁጥጥር ሥራው፣ በውክልና እና ምክር ቤታዊ የዲፕሎማሲ ተግባራት ረገድ በ2014 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ዐበይት ሥራዎች በተመለከተ፤ በጽሕፈት ቤታቸው ለመገናኛ ብዙኃን ባብራሩበት ወቅት ነው።

አፈ-ጉባዔው በዚህ ወቅት፤ ኢትዮጵያዊያን በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ ምክር ቤቱ በ2ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ በሠላም፣ ፀጥታ እና ደኅንነት ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን እንደሚያከናውን ከወዲሁ አስታውቀዋል።

ይህ ዕውን ይሆን ዘንድም፤ መላው ኢትዮጵያዊያን ከመንግስት እና ፀጥታ አስከባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን መታገል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ምክር ቤቱ ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎንም፤ ጊዜ በማይሰጣቸው ምጣኔ-ሀብታዊ በተለይም የኑሮ ውድነትን እና ሥራ-አጥነትን፣ የአገልግሎት ሰጪው ቀልጣፋ እንዲሆን ለማድረግ እና ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጄክቶች እንዲጠናቀቁ በቀጣይ ትኩረት እንደሚደረግባቸው፤ አፈ-ጉባዔው አመላክተዋል።

ምክር ቤቱ በባለፈው በጀት ዓመት የቁጥጥር እና ክትትል ዓቅሙን ለማጠናከር እና ተልዕኮዎቹን በብቃት ለመወጣት ለምክር ቤት አባላት በፖሊሲዎች እና ሕጎች እንዲሁም በምክር ቤቱ አሠራር ላይ ያተኮረ የዓቅም ግንባታ ስልጠና መስጠቱንም አስታውሰዋል።

በበጀት ዓመቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጨምሮ 14 አዋጆች እንደፀደቁም፤ አፈ-ጉባዔው አያይዘው ገልጸዋል።

በ ስሜነው ሲፋረድ