3.4 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ሚንስትሯ ገለጹ

--------------------------

(ዜና ፓርላማ) ሚያዚያ 2 2017 .ም፤ አዲስ አበባ፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በዘጠኝ ወራት ውስጥ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ክብርት ሚኒስትሯ / ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 23 መደበኛ ስብሰባው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን 2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የዳመጠ ሲሆን፤ የምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎች አቅርበው ክብርት ሚኒስትሯ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪያት ካሚል፣ በግብርናው፣ በአገልግሎት እና በኢንዱስትሪው ዘርፎች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠር መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በሀገር ውስጥና ውጭ ሀገራት ዜጎችን በማሰልጠን እና በማብቃት በዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተሰራው ስራ ውጤት ማምጣት መቻሉን ክብርት ሚኒስትሯ አያይዘው ገልጸዋል፡፡ 

ሀገራዊ ብልፅግናን እውን ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ሀገራዊ ዕገድትን ለማፋጠን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ክብርት ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

የሰው ሀብት ልማት፣ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (/) ተቋሙ የመንግስትን የአገልግሎት ማሻሻያ የሪፎርም ትግበራ፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጣራ እንዲሁም ተቋሙ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለሰራው ስራ በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

ለውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት እና በኢንዱስትሪው ዘርፍ በይበልጥ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቀጣይ ተኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (/) አስገንዝበዋል፡፡

የሥራና አሰሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር በተያያዘ እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (/) አሳስበዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤  ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ቴክኖሎጂን በመጠቀም በበይነ መረብ እየሰጠ ያለው አገልግሎት እና የሪፎርም  ስራዎች የሚበረታቱ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሁሉንም አካባቢዎች ታሳቢ ያደረገ ለዜጎች ፍታሃዊ የሆነ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባ፤ ወደ ውጭ ሀገራት የሚሰመሩ ዜጎች ሰብአዊ መብታቸውና ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት የምክር ቤት አባላት ዘስገንዝበዋል፡፡

ህግ እና ስርዓትን ተከትለው በማይሰሩ ኤጀንሲዎች ላይ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መውስድ  እንዳለበት የምክር ቤት አባላት አስገንዝበዋል፡፡

(በመኩሪያ ፈንታ)