null Culture, Tourism & Mass Media Affairs standing committee urged Ethiopian News Agency Board to give the necessary support & follow up to the agency.

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል፣ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  በኤጀንሲው በመገኘት የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሙለታ የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ አጠር ያለ ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል፡፡

በሪፖርቱም እንደገለጹት በተቋሙ ዕቅድ ላይ በየደረጃው ያለውን ሰራተኛ በማሳተፍና የጋራ በማድረግ ካስኬድ ተደርጎ እየተሰራበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በይዘት የስራ ክፍል ውስጥ የሚካተቱት የዜና ክፍሎች የአዲስ አበባና አካባቢው የዜና ዴስክ፣ የክልሎች የዜና ዴስክና የውጭ ቋንቋ የዜና ክፍሎች ያሉ ሲሆን በውጭ ቋንቋ ዕቅዳቸው ሰፊ ቢሆንም አረብኛና እንግሊዘኛ ላይ እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የፕሮዳክሽን ስራ በሚመለከት በየቀኑ በአማካኝ ከ5 እስከ 10 ዜናዎች ቪዲዮን ጨምሮ፣ ዶክመንተሪና ሌሎችንም፣ በቅርብ የተጀመሩ የሀብት ማመንጫ፣ የህዝብ አስተያየት ጥናቶች፣ የተለያዩ ኢቨንቶችን የማደራጀት ስራዎች እየሰሩ መሆኑንና በኢትዮጵያ ሚዲያ አዳዲስ የሚባሉ ስራዎችን ለመስራት ተቋሙ እየተደራጀ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የተቀናጀ የህዝብ ግንኙነት ስራ፣ የድህረ-ገጽና ኦንላየን ሚዲያ በቀን ከ15 እስከ 20 ዜናዎችን የሚያስተናገድ ሲሆን በአማካኝ በቀን ከ6 መቶ እስከ 7 መቶ ሺ ሰዎች ይጎበኙታል፡፡

በመደበኛ ድህረ-ገጽ በአማርኛው ከ25 እስከ 30 ሺህ ደንበኛ እንዳላቸው በእንግሊዘኛው  ደግሞ 15 ሺህ ደንበኛና በአረብኛ ከ30 እስከ 40 ሺ የሚደርስ መሆኑንና ጎብኚዎቹም በአብዛኛው መገናኛ ብዙሀን ሲሆኑ ተቋሙ የዜና ምንጭ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በአማካኝ በቀን ከሃያ አምስት እስከ ሰላሳ የሚሆኑ ዜናዎች እንዲዘጋጁም አክለዋል፡፡ አዲስ የፕሮጀክት ስራ፣ የመዋቅር ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን፣ የህግ ማዕቀፎችን የማሻሻል፣ ሀብት የማመንጨት ስራ የሚሰሩ መሆኑንና በየሳምንቱ የኢዲቶሪያል ቦርድ ግምገማ እንዲሁም በቀን ሁለት ጊዜ ኢዲቶሪያል ኮንፈረንስ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም አዳዲስ የክልል ቅርንጫፎች መክፈታቸውንና ተጨማሪ ለመክፈት ማቀዳቸውን ገልጸው የሰው ሀይል እጥረት፣ የግብአት፣ የደሞዝና የአበል ክፍያ አነስተኛ መሆንና መረጃ አለማግኘት ችግሮች እንደሚያጋጥሙም አክለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ኤጀንሲው በስትራቴጂክ እና አመታዊ ዕቅዱ ላይ ሁሉንም ሰራተኛ ማሳተፉ፣ የለውጥ ቡድኑ እንቅስቃሴ፣ በዜና ዝግጅት ተወዳዳሪና ውጤታማ ለመሆን በከፍተኛ ሁኔታ ዘገባዎችን በመዘገብ የተለየ ዜና በማዘጋጀት ለአድማጩ ተፈላጊና ተመራጭ ለመሆን ትልቅ የሪፎርም ስራ እየተሰራ መሆኑን በጥንካሬ አንስተው፤ በአጠቃላይ የኤጀንሲው ሲታይ ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከሰራተኛ ጥቅማ ጥቅም፣ ከአበልና ደሞዝ ጋር ተያይዞ መመለስ ያለባቸው ጉዳዮች መጓተታቸው፣ የተጠናው መዋቅር ተግባራዊ አለመደረጉ፣ የስራ አመራር ቦርዱ አሰፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ላይ ያሉ ውስንነቶች መሆናቸውን ጠቁመው፤ በሰራተኛውና በአመራሩ በኩል ጥሩ የለውጥ ጅምሮች ቢኖሩም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና ቋሚ ኮሚቴውም ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

Culture, Tourism & Mass Media Affairs standing committee urged Ethiopian News Agency Board to give the necessary support & follow up  to the agency.