(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 21፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የላይኛውን ጉደር ግድብ እና የመስኖ ልማት ፕሮጄክት ዝግጅት እና አፈጻጸም መሠረታዊ ችግር እንዲፈትሽ፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተጠየቀ።

ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ጥያቄ ያቀረበው፤ በቀድሞው የመስኖ ልማት ኮሚሽን፣ በአሁኑ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የላይኛው ጉደር ግድብ እና የመስኖ ልማት ፕሮጄክት ዝግጅት እና አፈጻጸም ረገድ የተከናወነውን የ2013 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ሰሞኑን በገመገመበት ወቅት ነበር፡፡

የላይኛው ጉደር መስኖ ልማት ፕሮጄክት በሚፈለገው መልኩ እየሄደ ላለመሆኑ እና ለመጓተቱ ዋነኛው መንስዔ የአዋጭነት ጥናቱ በአግባቡ አለመታየቱ መሆኑን የጠቆመው ኮሚቴው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መሠረታዊ ችግሩን ፈትሾ በትኩረት እንዲሠራ አሳስቧል፡፡

ኮሚሽኑ የመስኖ ውሃ የሚሄድበትን መስመር ዝርጋታ እንዲያከናውን ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ጋር ውል የተፈራረመው እ.አ.አ ሰኔ 24 ቀን 2019 እንደነበር ቋሚ ኮሚቴው መረጃ ጠቅሶ ገልጿል። ኦዲቱ እስከተከናወነበት ድረስ በነበረው ጊዜ የግንባታ ሥራው ከ45 በመቶ እስከ 50 በመቶ መድረስ የነበረበት ቢሆንም፤ እስከ ጥር 2013 ዓ.ም. የነበረው አፈጻጸም 6 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ መሆኑንም አስረድቷል፡፡

ለልማት ተነሺዎች ለንብረት ካሳ ክፍያ፣ ለመሬት ባለይዞታዎች ካሳ ክፍያ፣ በአጠቃላይ ለ16 ሺህ 231 ነዋሪዎች እንዲሁም ለዚህ ሥራ የተሰየመውን ኮሚቴ ውሎ አበል እና ስልጠና ጨምሮ ከተመደበው 571 ሚሊዮን 915 ሺህ ብር፤ እስከአሁን ለ1 መቶ 36 ሰዎች 2 መቶ 78 ሚሊዮን 9 መቶ 93 ሺህ ብር እንደተከፈላቸው፤ ቋሚ ኮሚቴው ግኝቱን መሠረት አድርጎ አስቀምጧል። ይህም ከመነሻ ጥናቱ ጋር ሲነጻጸር፤ 99 በመቶ የሚጠጉት ክፍያ የሚገባቸው የልማት ተነሺዎች እንዳልተከፈላቸው፣ ኮሚቴው ከዋና ኦዲተር ያገኘውን የኦዲት ግኝት መረጃ ተንተርሶ ጠቅሷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በኦዲት ግኝት ማስተካከያው መርኃ-ግብር መሠረት እስከ ሐምሌ 5፣ 2014 ዓ.ም. ድረስ የወሰዳቸውን የማስተካከያ ርምጃዎች የተመለከተ ሪፖርት ለኮሚቴያቸው እንዲያቀርብ ጠይቀዋል። ሪፖርቱ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር እና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ለሚከታተለው ቋሚ ኮሚቴ በግልባጭ ሊደርሳቸው እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

የተከበሩ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከላይኛው ጉደር መስኖ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን በመለየት፣ ክፍተቶችን በመሙላት፣ ጥፋተኛ በሆኑ ባለሙያዎች እና የሥራ ኃላፊዎች ላይ ርምጃዎችን ወስዶ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ሊያሳውቀን ይገባል ብለዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ክርስቲያን አክለውም፤ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሚያከናውናቸው የልማት ፕሮጄክቶች የአዋጭነት ጥናት የተሠራላቸው፣ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ የሚደረግባቸው እና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት እና ባለቤትነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ግንዛቤ ወስዶ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም ሰብሳቢው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከላይኛው ጉደር መስኖ ፕሮጄክት ጋር ተያያዥ በሆኑ የኦዲት ግኝቶች ማስተካከያ አፈጻጸም ረገድ፣ በየሦስት ወሩ ለቋሚ ኮሚቴው፣ ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት እና ለገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት እንዲያቀርብ አዘዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኦዲት ግኝቱን በ2015 በጀት ዓመት የዕቅድ ዝግጅት እንዲያካትትም አቅጣጫ ሰጥተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በላይኛው ጉደር የመስኖ ፕሮጄክት የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ሚኒስቴሩ በቂ ምላሽ ሰጥቷል ብሎ ስላልወሰደ፤ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ልዩ ኦዲት ሠርቶ ሪፖርት እንዲያቀርብ ሰብሳቢው አመላክተዋል። የኦዲት ግኝቱን መነሻ በማድረግ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ጉዳዮች ካሉም ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ አያይዘው አስገንዝበዋል፡፡

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎችም የሚፈለገውን ሥራ ለመሥራት ተቋሙ የዓቅም ውስንነት እንዳለበት፣ መጠናከር እንደሚገባው እና ማነቆዎች መፈታት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ መሥሪያ ቤታቸው አዲስ በመሆኑ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል። ቋሚ ኮሚቴው የሰጣቸውንም ግብረ-መልስ በግብዓትነት ተጠቅመው፤ የፕሮጄክቱ ችግር እንዲፈታ የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

ግኝቶች አስተማሪዎች በመሆናቸው ለቀጣይ ሥራዎቻቸው የጥንካሬ ምንጭ አድርገው መውሰዳቸውን ሚኒስትሯ ገልጸው፤ የካሳ ክፍያ ጉዳይ የአሠራር ክፍተቶች እንዳሉበት እና በቀጣይ መፈታት የሚችሉ በመሆናቸው፤ ከባለሙያዎች እና ከክልሎች ጋር በቅንጅት ሠርተው እንደሚፈቱት አመላክተዋል፡፡

በ መስፍን አለሰው