የሕይወት ታሪክ

የህይወትታሪክ፣ አቶ ቀለሙ ሙሉነህ ከእናታቸው ከወ/ሮ ዘውዴ ልመንህ ከአባታቸው ከሃምሳ አለቃ ሙሉነህ እምሩ በቀድሞው አገው ምድር አውራጃ በአንከሻ ወረዳ በምንጉላ ኪዳነምህረት ቀበሌ በ3/7/1959 ዓ.ም ተወለዱ። በቤተሰብ መልካም እንክብካቤ አድገው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአገው ግምጃቤት አንደኛና መለስተኛ ደረጃ ት/ቤት ከ1-8ኛ ክፍል ተምረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከ9-10ኛ ክፍል በዳንግላ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም ከ11-12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በቡሬ ሽኩዳዳ 2ኛደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል። በ1975 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው በ1976 ዓ.ም በጎንደር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በመምህርነት በሰርቲፍኬት ተመርቀው በቀድሞው ጎጃም ክ/ሀገር በቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ በቋሪት ወረዳ ተመድበው እስከ 1980 ዓ.ም በአንደኛ ደረጃ መምህርነት አገልግለዋል። በኋላም ወደ ትውልድ ቦታቸው ወደ አገው ምድር አውራጃ በመዘዋወር በባንጃ ወረዳ ተመድበው እስከ 1989 ዓ.ም በመምህርነት አገልግለዋል። በ1992 ዓ.ም በጎንደር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ትምህርታቸውን ለማሻሻል በዲፕሎማ ተከታትለው በኬምስትሪ በዲፕሎማ ተመርቀዋል። እንዲሁም ከባህርዳር ዩንቨርስቲ በ1999 ዓ.ም በኢኮኖሚክስ ዲግሬአቸውን በኋላም በ2004 ዓ.ም በኤክስኪውቲቭ ንግድ አስተዳደር (Executive Business Administration ) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቀዋል። አቶ ቀለሙ ሙሉነህ ከ1989 -2010 ዓ.ም ድረስ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተሹመው በመምሪያ ኃላፊነትና በምክትል አስተዳዳሪነት በመልካም ሥነ-ምግባር አገልግለዋል። እንዲሁም ከ3ኛው ዙር አስከ 5ኛው ዙር ድረስ ለሦስት ዙር የክልል ምክርቤት ተመራጭ በመሆን የህዝብ ውክልና በትጋት ተወጠዋል። ከ2011 መስከረም ወር ጀምሮ በአማራ ክልል ም/ቤት የኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪ፤ ከ2012 -17/5/2015 ዓ.ም የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ በመህን ሠርተዋል። ከጥር 17/2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የአማራ ክልል ገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራአስኪያጅ በመሆን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። አቶ ቀለሙ ሙሉነህ የሁለት ወንድና የሦስት ሴት ልጆች አባት ናቸው።