ምክር ቤቱ በአንቀጽ 55፣ አንቀጽ 70(1)፣ አንቀጽ 79(4)(ሐ)፣ አንቀጽ 82(2)(ሐ)፣ አንቀጽ 101፣ አንቀጽ 102፣ አንቀጽ 103 እና... የተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል።
የሕይወት ታሪክ
1. መሰረታዊ መነሻና የትምህርት ጉዞ
ዶ/ር አባስ ሀሰን የሱፍ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በምስራቅ ጉራጌ ዞን፣ ፣ በመስቃን ወረዳ፣ እምቦር ቀበሌ ገበሬ ማህበር መደን በሚባል የገጠር መንደር ከአርሶ አደር ቤተሰብ ተወልደው አድገዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በመስቃን ቆቶ ፍሰሃ ውልጊቾ መታሰቢያ እና በቡታጅራ መጀመሪያና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተከታተሉ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርታቸውን በቡታጅራ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል። ለከፍተኛ ትምህርት ባላቸው ጽናት ከዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እና ከአዲስ አበባ አልካን የጤናና ቢዝነስ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዎችን ያገኙ ሲሆን በከፍተኛ ጤና መኮንንነት (Senior Public Health Officer) ማዕረግ ተመዝግበው አገልግለዋል።። በመቀጠልም በቻይና ቤጂንግ በሚገኘው ዓለም አቀፍ ዝና ባለው ችንሁዋ ዩኒቨርሲቲ (Tsinghua University) በኢንተርናሽናል የህብረተሰብ ጤና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (Master's)፣ እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ በህብረተሰብ ጤና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን (PhD) አጠናቀዋል።
2. የሙያዊ፤የአመራርና የህዝብ አገልግሎት ጉዞ
ዶ/ር አባስ በጤናው ዘርፍ ከ16 ዓመታት በላይ በሰጡት አገልግሎት ከክሊኒካል እስከ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ የአመራርነትና እና የሥራ አስፈፃሚነት ኃላፊነቶች ላይ በብቃት አገልግለዋል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ጤና ጽሕፈት ቤት እና ጤና ቢሮ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመስራት ለጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራት እምርታዊ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል ። በጤና ሚኒስቴር የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር በመሆን የመጀመሪያውን ብሔራዊ ስፔሻሊቲና ሰብ-ስፔሻሊቲ የህክምና አገልግሎት ፍኖተ ካርታ እና የሰው ሠራሽ አካልና አጋዥ መሣሪያዎችና የተሃድሶ ህክመና እስትራቴጂ ቀረጻና ትግበራ መርተዋል። በአሁኑ ወቅት በጤና ሚኒስቴር የጤና ሥርዓት ኢኖቬሽንና ጥራት መሪ ሥራ አስፈፃሚ በመሆን ሀገራዊ የጤና ሥርዓት ኢኖቬሽን፤ጥራት፤ፍትሃዊነትና አመራር ማሻሻያዎችን እየመሩ ይገኛሉ።
3. ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ስኬቶች
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ሃሳብ አመንጪነት የተከናወኑ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በስኬት መርተዋል። ከእነዚህም መካከል የጤና ሚኒስቴርን የመጀመሪያ የጤና ኢኖቬሽን ዲፓርትመንት በማደራጀትና በመምራት፣ ብሔራዊ የጤና ኢኖቬሽን ማበልጸጊያ ማዕከልና የትግበራ ማዕከላትን እንዲሁም ስትራቴጂካዊ አጋርነቶችን በመገንባት በሃገራችን የጤና ሥርዓት ውስጥ የኢኖቬሽን ስራዎችን ቀረጻ በማድረግ፣ በመተግበር እና በመገምገም ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በተጨማሪም አካል ጉዳተኞች ጥራት ያለው የሰው ሠራሽ አካልና አጋዥ መሣሪያዎች እንዲያገኙ የሚያስችል የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከልን (EPOS) በአዲስ አበባ እንዲቋቋም አድርገዋል። በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘውን የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የማቋቋምና የማደራጀት ሥራን በስኬት የመሩ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ 7 ጤና ጣቢያዎች ውስጥ የእናቶችና ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚረዱ ድንገተኛ የቄሳር ክዋኔ (CS) መስጫ ክፍሎችን አቋቁመዋል። እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት ማዕከላት እንዲቋቋሙ በማድረግ ለታካሚዎች ሕይወት አድን ሕክምና ተደራሽ እንዲሆን አድርገዋል።
4. አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎና አመራር
በመላው አፍሪካ የጤና ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እንዲስፋፋ በሚሰራው የፓን-አፍሪካ መንግስታት የጤና ቴክኖሎጂ የሥራ ቡድን (HealthTech Hub Africa) በተባባሪ ሰብሳቢነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ከዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ባከናወኗቸው የለውጥ ሥራዎች የላቀ ዕውቅናዎችን እና ሰርተፊኬቶችን አግኝተዋል።
5. ማህበራዊ ትስስርና ዕይታ
ዶ/ር አባስ ከሙያዊ ኃላፊነታቸው ጎን ለጎን ከትውልድ ቀዬአቸውና ከማህበረሰባቸው ጋር ያላቸው ማህበራዊ መሰረትና ትስስር ጠንካራ ነው። በሃገራዊና አካባቢያዊ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የቦርድ አመራርነት፣ የልማትና የበጎ አድራጎት ተግባራት በመሳተፍ ለሃገራቸውና ለአካባቢያቸው ዕድገት የበኩላቸውን አሻራ እያሳረፉ ይገኛሉ። የትምህርት፣ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የጤና ጥራት ኢኖቬሽኖችን በማቀናጀት የኢትዮጵያን እና የአፍሪካን የጤና መጻኢ ዕድል በመቅረጽ ላይ ከሚገኙ አንጸባራቂ ምሁራን አንዱ ናቸው።
6. የብልፅግና ፖለቲካዊና ልማታዊ እይታዎች
የፓርቲውን ፖለቲካዊና ልማታዊ እይታዎች በተግባር በመተርጎም በሀገራዊ የጤና ሥርዓት ልማትና ለውጥ ጉዞ ላይ ታላላቅ ማህበረሰብ ተኮር አሰራሮችንና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ከሐሳብ እስከ መሬት በማድረስ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትና የፓርቲያችንን ራዕይ በተግባር የሚተረጉሙ፣ በዕውቀትና በልምድ የታነጹ፣ የህዝብን ችግር በቅርበት የሚረዱና በቅንነት በማገልገል ላይ የሚገኙ ከፍተኛ ባለሙያ እና የለውጥ መሪ ናቸው ፡፡