ምክር ቤቱ በአንቀጽ 55፣ አንቀጽ 70(1)፣ አንቀጽ 79(4)(ሐ)፣ አንቀጽ 82(2)(ሐ)፣ አንቀጽ 101፣ አንቀጽ 102፣ አንቀጽ 103 እና... የተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል።
የሕይወት ታሪክ
የግል የህይዎት ታሪክ
እኔ ደሴ አሰሜ ምትኩ ከአባቴ ከአቶ አስሜ ምትኩ ካሳ እና ከእናቴ ከወ/ሮ ላዋይ አስማረ ፈለቀ በቀድሞ ጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረታቦር አውራጃ በእስቴ ወረዳ፤ በአሁኑ ደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር በአንዳቤት ወረዳ መርጅና ጠንቆጥ ቀበሌ መርጅ ኢየሱስ ደብር ሰኔ 12 ቀን 1964 ዓ/ም ተወለድኩ፡፡
የወላጆቸ ሁለተኛ ልጅ ስሆን አስተዳደጌ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ለወላጆቸ እየታዘዝኩ እና ስራ እየረዳሁ ነው፡፡ዕድሜየ እንደደረሰ በጊዜው ወደ ትምህርት ቤት ባልገባም ለተወሰነ ጊዜ ከብት ከጠበኩ በኋላ ከመርጌታ ቸኮል የቄስ ትምህርት ገብቸ በመማር ፊደል መቁጠርና ንባብ ማንበብ ቻልኩ፡፡እንዲሁም የቄስ ትምህርት እየተማርኩ የጎልማሶች መሰረተ ትምህርት ቅዳሜ እና እሁድ በመማር አራቱን የሂሳብ ስሌቶች ለማወቅ ችየ ነበር፡፡
የጣቢያችን የመሰረተ ትምህርት መምህር የነበረው ደሳለኝ ምትኩ በትምህርት በነበረኝ ፍላጎትና ጉብዝና በቤተሰቦቸ ላይ ጫና አድርጎ ወደ ዘመናዊ/አስኳላ/ ትምህርት ቤት እንድገባ አስፈቀደልኝ፡፡በመሆኑም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ጃራገዶ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት፤ከ7ኛ እስከ 9ኛ ክፍል በቀድሞ በባሌ ክፍለ ሀገር በዶዶላ አውራጃ በአዳባ ወረዳ በአደባ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፤ከ10ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በደሴ ከተማ በሚገኘው የጢጣ ልዩ አዳሪ ት/ቤት የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ለመማር ችያለሁ፡፡በኢትዮጵያ ሲቭል ሰርቪስ ኮሌጅ በአካውንቲግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ፤በእንግሊዝ ሀገር በሚገኘው ክራንፊልድ ዩንቨርስቲ በፀጥታ ተቋማት አመራር/Security Sector Management/ ትምህርት የማስተርስ ዲግሪ በመከታተል ተመርቂያለሁ፡
በ1985 ዓ/ም ከወዘሮ የሽ አቸነፍ አደመ ጋር በአርማጭሆ ማሰሮ ደንብ ትዳር በመመስረት በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ አሁን ለደረስንበት ስኬት ለመብቃት ችለናል፡፡በማንኛውም ትዳር የሚያጋጥመው ፈተና በእኛ የትዳር ህይዎት ውስጥ የነበረ ቢሆንም ፈተናዎችን እየተጋፈጥን በማለፍ ሁለት ሴቶች እና አንድ ወንድ ልጅ በማፍራት በትዳራችን በመፅናት ደስተኛ ሆነን ኑረናል፡፡ከፈጣሪ የተሰጡን የስጋ ልጆቻችን ሰላማዊት ደሴ አሰሜ፤ቤተለሄም ደሴ አሰሜ እና አቤሜሌክ ደሴ አሰሜ በስርዓት በማሳደግ ለቁም ነገር እንዲደርሱልን በቻልነው አቅም የዎላጅነት ሀላፊነታችን በመወጣት ላይ እንገኛለን፡፡
በስራ ህይዎቴ ከ1983 ዓ/ም ጀምሮ የደርግን ስርዓት በመቃወም የኢህዴን/ኢህአዴግ አባል በመሆን ለኑሮ እና ለስራ ባልተመቹ ቦታዎች ሁሉ በመመደብ ህዝብን በቅንነት እና በታማኝነት አገልግያለሁ፡፡
በወረዳ፤በዞን እና በክልል በአመራርነት የተመደብኩባቸው የስራ ቦታዎች እና ሀላፊነቶች አስቸጋሪ የነበሩ ቢሆንም በወጣትነት ዘመኔ በሙሉ ቁርጠኝነት፤ በቅንነት እና በታማኝነት የህዝብ ኑሮ የተሻለ እንዲሆንና ለውጥ እንዲመጣ፤ሰላም እንዲሰፍን፤የህዝብ ንቃት ህሊና እንዲዳብር፤የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ባለኝ አቅም በርካታ ስኬታማ ስራዎችን ሰርቸ ውጤት አምጥቻለሁ፡፡
ከግንቦት 1983 ዓ/ም እስከ ጥቅምት 1984 ዓ/ም በሰሜን ጎንደር ዞን በላይ አርማጭሆ ወረዳ በካድሬነት አገልግያለሁ፡፡ከህዳር 1984 ዓ/ም እስከ ነሀሴ 1984 ዓ/ም በተመሳሳይ በሰሜን ጎንደር ዞን በታች አርማጭሆ ወረዳ በካድሬነት ሰርቻለሁ፡፡ከመስከረም 1985 ዓ/ም እስከ ጥቅምት 1998 ዓ/ም በሰሜን ጎንደር ዞን በታች አርማጭሆ ወረዳ በምክትል አስተዳዳሪነት እና በዋና አስተዳዳሪነት ህዝብን በፖለቲካ በማንቃት፤ሰላምና ፀጥታ በማስፈን፤ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት በማረጋገጥ፤የወረዳውን ዳር ድንበር ከሱዳን እና ከትግራይ ተስፋፊዎች በመከላከል ለህዝብ አገልግያለሁ፡፡
ከ1983 ዓ/ም እስከ 2018 ዓ/ም በስራ ሀላፊነት የቆየውባቸው እና ያስመዘገብኳቸው ውጤቶች በአጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
1ኛ.ከሰኔ 1983 ዓ/ም እስከ መስከረም 1998 ዓ/ም በሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር በላይ አርማጭሆ እና በታች አርማጭሆ ወረዳ በድርጅት እና በመንግስት የተለያዩ ሀላፊነቶች በመመደብ በአካባቢው ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን፤የህብተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል የኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዕድገት ለማምጣት የትምህርት፤የጤና፤የግብርና፤የውሃ፤የመንገድ የመሳሰሉ ተቋማትን በመገንባት ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ሀላፊነቴን በቅንነት እና በታማኝነት ተወጥቻለሁ፡፡
በአካባቢው በቆየውበት ጊዜ በተገነቡ ትምህርት ቤቶች የተማሩ ህፃናት ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰው ህዝባቸውን እና አገራቸውን ሲያገለግሉ በአይናችን ለማየት በቅተናል፡፡በሰው ጉልበት እና በጋማ ከብት የግንባታ ማቴሪያል ከአንድ ቀን በላይ አጓጉዘን ትምህርት ቤት በመገንባት፤እንዲሁም ቤት ለቤት ዙረን ወላጆችን አሳምነን ያስተማርናቸው ልጆች ዛሬ በተወለዱበት አካባቢ ባለሞያ እና አመራር ሁነው እያገለገሉ ናቸው፡፡ለህብረተሰቡ የጤና ተቋማትን በመገንባት፤በሽታን በመከላከል እና በማከም ጤንነቱ እንዲጠበቅ ለማድረግ ችለናል፡፡አርሶ አደሮች በባለሞያ እና በቴክኒኦሎጅ ታግዘው በማምረት የምርት ጭማሪ በማምጣት ኑሮአቸውን ለማሻሻል ችለዋል፡፡በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የእንሰሳት ሀብት የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ህዝቡ የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
እንዲሁም በአካባቢው ሰላምን በማስፈን ለስራ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረግ ጉልህ ሚና ተጫውቻለሁ፡፡በግብርና እና በንግድ ስራ ውጤታማ ሁነው ወደ ትልልቅ ባለሀብትነት የተሸጋገሩ በርካታ የአካባቢው ልጆች ለመፍጠር ተችሏል፡፡በወረዳው የነበረውን የርዕስ በዕርስ ግድያ፤ሽፍትነት፤ህገወጥነትን በመከላከል በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም በማስፈናችን ህዝቡ የቀጣይ ዘላቂ ህይወት እና ተስፋ እንዲኖረው አድርገናል፡፡
የሱዳን መንግስት በኢትዮጵያ የነበረውን የዕርስ በርዕስ ግጭት በመጠቀም ድንበር ተሻግሮ ደን በመመንጠር እና እርሻ እያረሰ ሲጠቀምበት የነበረውን የአርማጭሆ የእርሻ እና የደን መሬት በማስለቀቅ ጉልህ ስራ ሰርቻለሁ፡፡
2ኛ.ከጥቅምት 1998 ዓ/ም እስከ የካቲት 1999 ዓ/ም በደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር የፀጥታ መምሪያ ሀላፊ በመሆን አገልግያለሁ፡፡
3ኛ.ከየካቲት 1999 ዓ/ም እስከ ህዳር 14/2009 ዓ/ም በአማራ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ በምክትል ቢሮ ሀላፊ እና በቢሮ ሀላፊነት በመመደብ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ፤የህብረተሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል በማስፋፋት፤ከአጎራባች ክልሎች እና ከሱዳን ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር የክልሉና የሀገራችን ጥቅሞች ለማስከበር ውጤታማ ስራ ለመስራት ችያለሁ፡፡
3ኛ.ከታህሳስ 2009 ዓ/ም እስከ ጥቅምት 2014 ዓ/ም የክልሉን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሁኘ በመመደብ ኮርፖሬሽኑን በአዲስ በማቋቋም እና የፓርኮችን መሰረተ ልማት በመገንባት በልማት ዕድገት የበኩሌን ድርሻ ተወጥቻለሁ፡፡ በበጀት መጠንም ይሁን በስራ ስፋት በክልሉ ትልቅ የሆነውን የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና የገጠር የሽግግር ማዕከላት ፕሮጀክቶች ግንባታ በማጠናቀቅ እና በማስመረቅ ሀላፊነቴን በብቃት ተወጥቻለሁ፡፡የጎንደር አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጎንደር ዩንቨርስቲ ምሁራን በማስጠናት የቦታ መረጣ እንዲካሄድ በማድረግ ስራ ለማስጀመር ችያለሁ፡፡
4ኛ.ከመጋቢት 2014 ዓ/ም እስከ ነሀሴ 2018 ዓ/ም በቢሮ ሀላፊ ደረጃ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር መሰረተ ልማት ጉዳዮች አማካሪ በመሆን እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡በመሆኑም በተመደብኩበት ሀላፊነት በክልሉ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ከሚመለከታቸው የፌድራል እና የክልሉ የመሰረተ ልማት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
እንዲሁም በ4ኛው እና በ5ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በእስቴ ቁጥር 3 ምርጫ ክልል በሁለት ዙር ለክልል ምክር ቤት በመመረጥ ለ10 ዓመት የህዝብ ድምፅ በመሆን አገልግያለሁ፡፡የባህር ዳር ዩንቨርስቲ፤የክልሉ ፍትህ ማሰልጠኛ ኢንስቲትት እና የህብር ኮንስትራክሽን የቦርድ አባል በመሆን ተቋሞች ተግባርና ሀላፊነታቸውን እንዲዎጡ አመራር ሰጥቻለሁ፡፡በአሁን ወቅትም የገንዳ ውሃ ጥጥ መዳመጫ ሀላፊነቱ የግል ድርጅት የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡