ምክር ቤቱ በአንቀጽ 55፣ አንቀጽ 70(1)፣ አንቀጽ 79(4)(ሐ)፣ አንቀጽ 82(2)(ሐ)፣ አንቀጽ 101፣ አንቀጽ 102፣ አንቀጽ 103 እና... የተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል።
የሕይወት ታሪክ
የሕይወት ታሪክ በአማርኛ
እኔ ሁሴን ሰይድ አሊ ከአባቴ አቶ ሰይድ አሊ ይማም እና ከእናቴ ወ/ሮ አስረስ አበጋዝ መንሹ በ1960 ዓ.ም. በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን በተሁለደሬ ወረዳ በ014 ዋሂሎ ቀበሌ ውልቆ በምትባል ትንሽ መንደር ተወለድኩ።
በቤተሰባችን ውስጥ አራተኛ ልጅ ሲሆን ሁለት ወንድሞችና ሦስት እህቶች አሉኝ።
ወላጆቼ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ በመሆናቸው የልጅነት እድገቴን በግብርና ሥራ በመሳተፍና በትምህርት ቤት በመማር አሳልፌያለሁ።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን በዋሂሎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በሀይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ።
የከፍተኛ ትምህርቴን በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች በመከታተል በ1987 ዓ.ም. ከደሴ መምህራን ትምህርት ተቋም በመምህርነት በሰርቲፊኬት.
በ1997 ዓ.ም. ከጎንደር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በሂሳብ ትምህርት ዲፕሎማ አግኝቻለሁ።
በመቀጠልም ከወሎ ዩኒቨርሲቲ በ2008 ዓ.ም. በማኔጅመንት እና በ2012 ዓ.ም. በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የሁለተኛ ዲግሪዎችን አግኝቻለሁ።
የእኔ የቤተሰብ ህይወት በ1990 ዓ.ም. ትዳር በመመሥረት የሶስት ወንዶችና የአራት ሴት ልጆች በአጠቃላይ የሰባት ልጆች አባት ሆኛለሁ።
የሥራ ሕይወትና የሀገልግሎት ልምድ በተመለከተ፦ በ1978 ዓ.ም. በቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት በምድር ጦር አባልነት በመቀላቀል ጀመርኩ። እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ለስድስት ዓመታት በውትድርና ሀገሬን አገልግያለሁ።
በ01/11/1987 ዓ.ም. በመምህርነት ተቀጥሬ በአማራ ክልል፣ በደቡብ ወሎ ዞን፣ በከላላ ወረዳ በተለያዩ አንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት ለአስራ አንድ ዓመታት አገልግያለሁ።
ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ በከላላ ወረዳ በቀድሞው የአቅም ግንባታ ጽ/ቤት ኃላፊነት፣ እንዲሁም በከላላ ወረዳ የቀድሞው ብአዴን ፓርቲ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ እና ኃላፊ በመሆን በኃላፊነት ደረጃ ለሰባት ዓመታት አገልግያለሁ።
ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ደቡብ ወሎ ዞን፣ ተሁለደሬ ወረዳ ተዛውሬ በወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ በቀድሞው ብአዴን ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ እንዲሁም የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አገልግያለሁ።
ይህንን የአመራር አገልግሎት ከመጀመሪያ ዲግሪዬ የትምህርት ቆይታ ጋር ጨምሮ በአጠቃላይ ለሰባት ዓመታት በወረዳው አገልግያለሁ።
በመቀጠል በአማራ ክልል በደሴ ከተማ አስተዳደር በወዛወር በቧንቧ ውሃ ክፍለ ከተማ በቀድሞው ብአዴን ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና በዋና ሥራ አስፈፃሚነት እንዲሁም በደሴ ከተማ አስተዳደር በተርኒኪ ዋና ሥራ አስኪያጅነት በመሥራት ከሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ቆይታዬ ጋር ጨምሮ ለሰባት ዓመታት አገልግያለሁ።
ከሐምሌ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በደሴ ከተማ የኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ በመሆን እያገለገልኩ እገኛለሁ።
በአጠቃላይ ከሠላሳ አንድ ዓመት በላይ በሥራ ሕይወቴ በተለያዩ የመንግሥት፣ የትምህርትና የአመራር ኃላፊነቶች በትጋትና በታማኝነት አገልግያለሁ። በዚህ የሥራ ዘመንም ከተለያዩ አካላት የምስጋናና የአፈፃፀም ማረጋገጫ ሰርተፊኬቶችን አግኝቻለሁ።
በ2018 ዓም ኢትዮጵያ በተካሄደው 7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተሁለደሬ ወረዳ ቁጥር አንድ የምርጫ ክልል የብልፅግና ፓርቲን በመወከልና በፓርቲው እጩነት ተወዳድሬ በአብላጫ ድምፅ በማሸነፍ ተመርጫለሁ።
ይህ ድል በሕዝቡ የተሰጠኝን እምነትና ኃላፊነት በአግባቡ እንድወጣ የሚያነሳሳኝ ታላቅ እድል ነው።
በመሆኑም ለሀገሬና ለመረጠኝ ሕዝብ የሚጠበቅብኝን ኃላፊነት በታማኝነት፣ በትጋትና በተጠያቂነት ለመወጣት በቁርጠኝነት ተዘጋጅቻለሁ።
አጠቃላይ የሕይወት ጉዞዬ ከግብርና ቤተሰብ የልጅነት ሕይወት ጀምሮ በውትድርና፣ በትምህርት፣ በአመራርና በሕዝብ አገልግሎት ያለፈ ሲሆን በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ያካበትኩትን ልምድና ዕውቀት ለሀገሬና ለሕዝቤ የበለጠ ጥቅም ለማዋል ቁርጠኛ ነኝ።