ምክር ቤቱ በአንቀጽ 55፣ አንቀጽ 70(1)፣ አንቀጽ 79(4)(ሐ)፣ አንቀጽ 82(2)(ሐ)፣ አንቀጽ 101፣ አንቀጽ 102፣ አንቀጽ 103 እና... የተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል።
የሕይወት ታሪክ
የዶ/ር ኢንጂነር ጥላሁን ኤርዱኖ የህይወት ታሪክ
ዶ/ር ኢንጂነር፣ ረዳት ፕሮፌሰር፣ ጥላሁን ኤርዱኖ እንደ ምሁር ከሚታወቅባቸው ሙያዊና የአመራር ብቃቶች ሲዘረዘሩ: የቅየሳና ካርታ ሥራ ኤክስፐርት መሐንዲስ፣ ጂኦግራፈር፣ አስተማሪ - ተመራማሪ፣ አማካሪ፣ መጽሐፍ ደራሲ፣ የትምህርት አመራር፣ የሙያ ማህበር መሥራች መሪ፣ የህዳሴ ግድብ መሪ ሀሳብ አፍላቂና አቅራቢ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነውን የሰርቬይንግ ቴክኖሎጂ ሥርዓተ ትምህርት ቀራጭ፣ የህብረተሰብ አገልግሎት ሰጭ፣ አሰልጣኝ ወዘተ ሲሆን፣ በእነዚህና በመሳሰሉት የኃላፊነት ቦታዎች አገሩን በቅንነትና በፍጹም ታማኝነት ለ34 ዓመታት ያገለገለ ባለሙያ ሲሆን፣ ለዚህ ሁሉ ልዩ ልዩ አገራዊና ተቋማዊ አስተዋጽኦው ከተለያዩ መ/ቤቶች ዋንጫ፣ ሜዳሊያ፣ የምስክር ወረቀት፣ የዕውቅናና የምስጋና ደብዳቤዎችንና ሌሎች ሽልማቶችን አግኘቷል። ዝርዝሩን ከCVው ማግኘት ይቻላል።
1. የልጅነት ህይወት
ዶ/ር ጥላሁን ከአባቱ ከአቶ ኤርዱኖ ሐንቄቦና ከእናቱ ከወ/ሮ ወርቅነሽ ወ/ማሪያም በቀድሞ ሸዋ ክ/ሐገር በጊዳሻ ቀበሌ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1956 ተወለደ። የዶ/ር ጥላሁን ኤርዱኖ የልጅነት ህይወት ከብዙዎች ኢትዮጵያውያን የተለየ አልነበረም። ምንም እንኳ ወላጅ አባቱ ከትምህርቱ ውጭ ምንም እንዳይሰራ ቢፈልጉም ለቤተሰቡ አንጋፋ በመሆኑ ከትምህርቱ ጎን ለጎን በትርፍ ጊዜው ወላጆቹን ከብቶችን በማሰማራት፣ ማገዶ በመሰብሰብ፣ እርሻ በማረስ ወዘተ እያገዘ አድጓል።
2. የዶ/ር ጥላሁን የመጀመሪያና 2ኛ ደረጃ ትምህርት
ዶ/ር ጥላሁን ከተማረባቸው ት/ቤቶች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ መንፈሳዊ ት/ቤት (2 ዓመት) በቀን የ1 ሰዓት መንገድ እየተጓዘ፣ መራቢቾ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት (4 ዓመት) በቀን 2 ሰዓት እየተጓዘ፣ ሞርሱጦ መ/2ኛ ት/ቤት (2 ዓመት) በሳምንት 9 ሰዓት እየተጓዘ፣ ዋቸሞ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት (4 ዓመት) በወር 2 ቀናት እየተጓዘ የተማረባቸው ይገኙበታል።
3. የኮሌጅ ትምህርትና የሥራ ዓለም
ዶ/ር ጥላሁን እ.ኢ.አ በ1973 ዓም የESLCE ፈተና ወስዶ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያበቃ ውጤት በማምጣት እ.ኢ.አ. በ1974 ዓ/ም አዲስ አበባ በሚገኘው የኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ገብቶ ጂኦግራፊን በ1ኛ ታሪክን በ2ኛ ነት ተምሮ አጠናቀቆ በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህርነት በከፍተኛ ውጤት ተመርቀ። በመቀጠል በዚያን ዘመን አጠራር በሰሜን ወሎ በኮረም አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በመምህርነት ተመደበ። ለ3 ዓመታት ያህል በተማሪዎቹ እየተፈቀረ በመምህርነት የቀጠለው ዶ/ር ጥላሁን በ1978 ዓ/ም የውጭ ትምህርት ዕድል ተወዳድሮ አገኘ።
4. ከፍተኛ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ምህንድስና ትምህርት
በ1979 ዓ/ም ራሺያ የገባው ዶ/ር ጥላሁን ከሞስኮ በ135 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው ካሊኒን ከተማ በሚገኘው የካሊኒን መታሰቢያ ፖሊቴክኒክ ኢንስቲቲዩት ተመደበ። የአንድ ዓመት የመሰናዶ ትምህርቱን አጠናቆ በ1980 ዓ/ም ሞስኮ በሚገኘው 'Moscow Institute of Engineers in Geodesy, Airphotography, & Cartogrphy' ተመደበ። የሞስኮም ሆነ የካሊኒን የዓየር ጸባይና የበረዶ ዝናብ ለዶ/ር ጥላሁን ፈታኝ ነበር። በተደጋጋሚ በኒሞኒያ ተጠቅቷል። ያም ሆኖ በርትቶ በመማር በ1984 ዓ/ም የማስተርስ ዲግሪ የምርምር ርዕሱን (Thesis) የኢትዮጵያን ት/ቤቶች መሠረታዊ የጂኦግራፊ ትምህርት ጉድለትን ለማስወገድ በማሰብ በ"Childrens Cartography በተለይም በ School Atlas Design & Compilation ሰርቶ አቅርቦ በከፍተኛ ውጤት ሲመረቅ የPhD ትምህርቱን በዚያው እንዲቀጥል ግብዣ ቢቀርብለትም ትቶ በዚያው ዓመት ወዳገሩ ተመለሰ።
5. የመንግሥት ለውጥና የእነ ዶ/ር ጥላሁንና ሌሎች መሰሎች ፈተና
የደርግ መንግሥት ተበትኖ የኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣን በያዘበት ሁኔታ በውጭ አገራት ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ አገራቸው የተመለሱት ባለሙያዎች በአገር ውስጥ የተመረቁት ጨምሮ ያዩት ፈተና እጅግ ከባድ ነበር። ፈተናው ሁሉ ከወያኔ ኢህአዴግ የዘር ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነበር። ፈተናው የጀመረው የዘር ፖለቲካ ለማይደግፉ ምሩቃን የሥራ ዕድል ዝግ በማድረግ ነበር። ይህን ፈተና ለመሻገር በማሰብ የውጭም፣ የአገር ውስጥም ምሩቃን በአንድነት የመሠረቱት ለምለሚቱ ኢትዮጵያ ሁለገብ የልማት ድርጅት (ለኢሁልድ LEADO) የተባለው ፖለቲካዊ ያልሆነ ድርጅት የመጀመሪያው መሪ/ሊቀመንበር ሆኖ የተመረጠው ዶ/ር ጥላሁን ያየው ፈተና የተለየ ነበር። ምሩቃኑ በማህበሩ ጥላ ሥር ሆነው በየሙያው ተከፋፍለው ለራሳቸውና ለሌሎች ዜጎች ሥራ ለመፍጠር አስበው ያጠኗቸው እጅግ በርካታ ፕሮጀክቶች የወቅቱ መንግሥት የተለያዩ መ/ቤቶች ተቀብለው የውኃ ሽታ በማድረግ ለባለሀብቶች አሳልፈው በመስጠት ተጠቀሙበት። ማህበሩም ለመፍረስ ተገደደ። ዶ/ር ጥላሁንም አ/አ በሚገኘው የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት እያለ እንዳይቀጠር በመደረጉ ሥራ ፍለጋ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ አመራ።
6. ዶ/ር ጥላሁን በደቡብ ኢትዮጵያ ውሀ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ (ማዕድን መምሪያ)
በሰኔ 1986 ዓ/ም በተጠቀሰው መምሪያ የቅየሳና ካርታ ሥራ ክፍል ኃላፊነት ላይ የተመደበው ዶ/ር ጥላሁን በወቅቱ የተረጋጋ መንግሥት ስላልነበር ብቻ ሳይሆን የተመቻቸ የሥራ አካባቢ ባለመኖሩ (ቢሮዎች በአብዛኛው የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ነበሩና።) በዚህና ተያያዥ ብዙ ችግሮች የተነሳ ሳይሰሩ ወር እየቆጠሩ ደመወዝ መቀበል ከባድ ፈተና የሆነበት ዶ/ር ጥላሁን የክልሉን የማዕድን ስርጭት የሚያሳይ ካርታ አቅዶ መንደፍ ጀመረ። በመምሪያው በተለይም በማዕድን ቡድን ውስጥ አብረውት የሚሠሩትን 5 ጂኦሎጂስቶች የካርታ አሠራር ጽንጸ ሀሳብ ማጎናጸፍ ቻለ። ትንሽ ቆይቶም ሁኔታዎች እስቲስተካከሉ ድረስ ለጂኦሎስቶቹ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በማሰብ ለቢሮ ኃላፊው በማማከር ለመዕድን ሚኒስቴር ደብዳቤ እንዲጻ በማድረግ ራሱ ደብዳቤውን ይዞ ማዕድን ሚኒስቴር በማቅረብ አንድ ኦራል መኪና ሙሉ ለማዕድን ጥናት ሥራ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን ጭኖ መመለስ ቻለ። የባለሙያዎቹ ቁጭ ብሎ ሳይሰሩ ደመወዝ መቀበል ቆመ ወደሥራ ተገባ። ዘርፉ ተበረታታ ከማዕድን የሚገኘውም ገቢ በእጅጉ ጨመረ። ዶ/ር ጥላሁን የማዕድን ሚኒስቴርን የእንግሊዝኛ ደንብ ወደ አማርኛ በመተርጎም ለህዝብ ግልጽ እንዲሆን አደረገ። ዶ/ር ጥላሁን በዚሁ መ/ቤት ለ3 ዓመት ተኩል ከአገለገለና በርካታ አስተዋጽኦዎችን ካበረከተ በኋላ ወደ ማስተማር ሥራው ለመመለስ ወሰነ።
7. ዶ/ር ጥላሁን በናዝሬት ቴክኒክ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ (ናቴመትኮ-NCTTE)
ዶ/ር ጥላሁን በጥቅምት 1990 ዓ/ም በናቴመትኮ (NCTTE) በመመህርነት ተቀጠረ። በዚህ ተቋም ውስጥ በቅየሳና ካርታ ሙያው ዘርፍ በቂ መምህር ባለመኖሩ መምህር ጠፍቶ እጅግ ብዙ የተንከባለሉ በጥቅሉ የቅየሳና ካርታ ሥራ ትምህርት ኮርሶች ስለነበሩ የዶ/ር ጥላሁን የማስተማር ሥራ ጫና ከሚገመተው በላይ ቢሆንም ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ ሁለት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሰርቬይንግ ትምህርት ክፍል ኃላፈ ሆኖ በመምህራን ተመረጠ። ከነበሩት የሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ነባሮቹን የሰርቬይንግ ቴክኖሎጂ ዲፕሎማ ፕሮግራምና የሰርቬይንግና ድራፍቲንግ ዲግሪ ፕሮግራም ካሪኩለም በሚገባ ለማሻሻል በቅቷል። በቀን፣ በማታ፣ በሳምንት መጨረሻ ፕሮግራሞች የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በአገሪቱ እጅግ ከፍተኛ የነበረውን የቅየሳና ካርታ ሥራ ባለሙያዎች እጥረት ለመሙላት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። የትምህርት ክፍሉ ተፈላጊነትም እየጨመረ መጣ። በተለይ ኮሌጁ ያለበት የአዳማ ከተማና አካባቢው ህብረተሰብ የክልሉ አስተዳደር በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ ማድረግ ተቻለ። ያም ሆነ የአገሪቱ ፍላጎትና ኮሌጁ የሚያስመርቃቸው ተማሪዎች ልዩነት የትየሌሌ ነበር።
8. የናቴመትኮ/NCTTE ወደ አዳማ ዩንቨርስቲ መሸጋገርና የዶ/ር ጥላሁን አስተዋጽኦ፣
NCTTE ወደ አዳማ ዩንቨርስቲ ሲሸጋገር ዶ/ር ጥላሁን በሚመራው ት/ክፍል ሶስት ዋና ዋና ችግሮች ነበሩ። እነዚህም ከፍተኛ የመምህራን እጥረት፣ ለፊልድና ለላበሩም ትምህርት የሚያስፈልጉ የላብ መሣሪያዎች እና የዲግሪ ካሪኩለም አለመኖር ነበሩ። እነዚህ ችግሮች ባሉበት እንዳሉ ከኮሌጅ ወደ ዩንቨርስቲ የሚሻገርበት ርግጠኛው ሰዓት ሲደርስ ሌላ 4ኛ ችግር ተከሰተ። ይህውም በአገሪቱ የኮንስትራክሽን ሴክተር እድገት ቡም ተፈጠረ። በዚህም የተነሳ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ 5 አሉ የተባሉ መምህራን በቀረበላቸው አጓጊ ደመወዝ የተነሳ ሥራቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸው ነበር። የት/ክፍሉ ኃላፊ የዶ/ር ጥላሁን ኤርዱኖ ሌላኛው ፈተና ከዚህ ጀመረ። ናቴመትኮ ከነበሩት የቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍሎች ሁሉ በአገር አቀፍ መሠረተ ልማት እድገት ላይ እጅግ ጠቃሚ የሆነው ት/ክፍል ሊዘጋ መሆኑ ታየው። በአገሩ ዕድገትና በሙያው ክብር የማይደራደረው ዶ/ር ጥላሁን ራሱ በ3 እጥፍ ደመወዝ ቢለመንም ት/ክፍሉን ዘግቶ መውጣት አልፈቀደም። ብቻውም ቢሆን ካሪኩለሙን ቀርጾ ለመተግበርና የተማረበትን የኢትዮጵያ ህዝብ ዕዳ ለመክፈል ወሰነ። አደረገውም። ካሪኩለሙ ለአገር አቀፍ ኮንፈረንስ ሲያቀርብ በአገቱ ያሉትን የቴክኖሎጂው ዘርፍ ችግሮችንና የመፍትሔ ሀሳቦችን በግልጽ አቀረበ። የተዛማጅ ሴክተር ተወካይ ሚኒስትሮች ችግሮቹንና መፍትሔዎቹን በከፍተኛ ሁኔታ ተቀበሉት። ያሉት የማስተማሪያ መሣሪያዎችን ከውጭ አገር ባለሙያ አስመጥቶ በማስጠገን፣ ተዛማጅ መሣሪያ አምራቾችን ዕርዳታ በመጠየቅ፣ የሌሉትን በማስገዛት፣ የ3.9 ሚሊዮን ብር መሣሪያ አስገዝቶ ሥራ በመጀመር ለ2 ዓመታት ሌት ተቀን እየሠራ አብዛኛውን ኮርስ ብቻውን እያስተማረ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያውን የሰርቬይንግ ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረግ አንድ ባች እዚያው አስመርቆ ጎበዝ ተማሪዎቹን አስቀጥሮ፣ በደመወዝ ጭማሪ ተበረታትተው ከወጡት መምህራን የተወሰኑትን መልሶ ቀጥሮ የት/ክፍሉን የሰው ኃይል እጥረት ማቃለል ቻለ። ካሪኩለሙም በተለያዩ የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መተግበር ጀመረ። ከዚህ ሁሉ የሰባት አመታት ያላሰለሰ ጥረትና ውጤት በኋላ በተመሳሳይ የሙያ መስክ የ2ኛ ዲግሪ ካሪኩለም እንዲከፈቱና እንዲስፋፉና የሴክተሩን የሰው ኃይል እጥረት በመቅረፍ የአገሪቱን የልማት እንቅስቃሴ ለማገዝ ለ3ኛ ዲግሪ ስኮላርሽፕ አመልክቶ ተፈቀደለት።
9. የዶ/ር ጥላሁን የPhD ትምህርት በሞስኮ የጂኦዴዚና ካርቶግራፊ የመንግሥት ዩንቨርስቲ
በ1998 ዓ/ም ታህሳስ ወር ሞስኮ የገባው ዶ/ር ጥላሁን ቀደም ሲል በማስተርስ ቴሲስ ፕሮግራም ጥናቱ ወቅት የጀመረውውን ለተለያየ ትምህርት ደረጃ ተማሪዎች አጋዥ መጽሐፍ እንዲሆን ያሰበውን (The Concept of Childrens Atlas) ርዕስ ወደ PhD ጽሑፍ በማሳደግ አጥንተው ጨርሰው በአቀረቡት የፒኤችዲ ጽሑፍ (PhD Dissertation Defence) እጅግ በጣም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በ1992 ወደ ነበረበት አዳማ ዩንቨርስቲ ተመለሰ። ዶ/ር ጥላሁን ሞስኮ ሲገባ ወደ KG ያመራችው ልጁን ለመርዳት በማሰብ ሌት ተቀን ሰርቶ ከ3 ዓመታት ቀድሞ ጨርሶ ሲያበቃ የመጨረሻውን የመመረቂያ ጽሑፍ አቅርቦ ባጠናቀቀ ማግሥት ዲሰርቴሽኑ ከነላፕቶፑ ብቻ ሳይሆን backup ፋይሉ ጭምር መጥፋቱና ያንን መልሶ ለመጻፍ ያደረገው ውሳኔ ዶ/ር ጥላሁን መቼም የማይረሳው ሆኖ አልፏል። ከዚህ ችግር ለመውጣት ያገዙትን ላፕቶፕ ኮምፕዩተር ገዝተው የሰጡትን ራሺያውያን ጓዶቹንና መምህራኖቹን ያመሰግናል።
10. የአዳማ ዩንቨርስቲ ወደ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መሸጋገርና የዶ/ር ጥላሁን ኤርዱኖ አስተዋጽኦ
በ2000 ሚሌኒየም ዓ/ም የፒኤችዲ ትምህርቱን አጠናቆ ወዳገሩ ሲመለስ ዶ/ር ጥላሁንን የጠበቀው በአንድ እጅግ ጠንካራ ጀርመናዊ የሚመራ ዩንቨርስቲ ሲሆን፣ ዩንቨርስቲውን ከአዳማ ዩንቨርስቲ ወደ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲ ለማሸጋገር እጅግ ከፍተኛ እልህ አስጨራሽ ትግል በሚደረግበት ወቅት ነው።
ዶ/ር ጥላሁን ዩንቨርስቲውን እንደተቀላቀለ በሲቪል ኢንጂነሪንግና አርክቴክቸር ዲፓርትመንት መምህራን የት/ክፍሉ (ኋላ ት/ቤት ሆኗል) መሥራች ኃላፊ እንዲሆን እርሱ ራሱ በሌለበት በከፍተኛ ድጋፍና ድምጽ ተመረጠ።
ዶ/ር ጥላሁን ይህን ክፍል ከአጠናከረና ለ6ቱም የምህንድስና ትምህርት ሰክሽኖች አስፈላጊ የሆኑ ሥርዓተ ትምህርቶችን በ2 ዓመታት ውስጥ አስጠንቶና አጥንቶ እንዳጠናቀቀና ሌሎች አያሌ ስኬቶችን ከአስመዘገበ በኋላ ለምርምርና ህትመት ቢሮ ዳይሬክተርነት በወጣው ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ በመወዳደር አሸንፎ ምርምርና ህትመት ቢሮ (RPO) ዳይረክተር ሆነ። ከተወሰኑ ወራት ቢሮውን የማጠናከር ሥራ በኋላ የቢሮው ሥራ መሥፋት አለበት በሚል የቢሮው ስያሜ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ቢሮ (Knowledge & Technolwgy Interchange) ተብሎ ተሰየመ። ዶ/ር ጥላሁንም የቢሮው መሥራች ዳይሬክተር ሆኖ በዚያው ቀጠለ። እጅግ በርካታ የምርምር ሥራዎች እየቀረቡና እየተገመገሙ ባለበት፣ ከበርካታ ባለድርሻ አካላትና ከሚመለከታቸው የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመን እየሠራን ባለበት ኢትዮጵያውያን የዩንቨርስቲው የአመራር አባላት ከጀርመናዊያን አመራሮች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ነገሮች ተበለሻሹ። ዶ/ር ጥላሁንም በተደራራቢ ከፍተኛ የሥራ ጫና የተነሳ ታሞ 25% የአካል ጉዳተኛ ሆኖ የዳይሬክተርነት ቦታውን ለቆ መመራመሩና የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ማስተማርና ማማከር ቀጠለ። ጀርመናዊያን አመራሮችም አገራቸው ገቡ።
11. የዶ/ር ጥላሁን ጡረታ መውጣት
ዶ/ር ጥላሁን ለ28 ተከታታይ ዓመታት በከፍተኛ ትጋትና ብቃት ከሰራበትና ከፍተኛ ልዩ ውጤት ካስመዘገበበት እንዲሁም ከፍተኛ የሲኒየር መምህርንና አማካሪዎች እጥረት ካለበት ዩንቨርስቲ በቀላሉ ያለፍላጎቱ ካለምንም ጥፋት ሊሰናበት እንደሚችል አስቦት አያውቅም ነበር። ከምክንያቶቹ አንዱና ዋነኛው በማስተማርም ሆነ በማማከር የእርሱን ያህል ልምድ ያለው ውጤታማ መምህር በት/ክፍሉ አልነበረምና ነው። ነገር ግን ቀኑ ተቆጥሮ ሆነ። ለ28 ዓመታት ያካበተውን ልምድ ተጠቅሞ ለትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች መጽሐፍ ለመጻፍ አገሩን የበለጠ ለማገልገል እያሰበ እያለ የወጠነው ዉጥን ድንገት ውኃ በላው። ሆድ ይፍጀው ነው ነገሩ።
12. የዶ/ር ጥላሁን ጡረታ መውጣትና ዩኒቲ ዩንቨርስቲ
ዶ/ር ጥላሁን ጡረታ ከወጣ በኋላ በቋሚነት ሥራ የጀመረው በዩኒቲ ዩንቨርስቲ አዳማ ካምፓስ ሲሆን የተሰጠው የኃላፊነት በተባባሪ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ደረጃ ሲሆን ዋናው ተልዕኮ በዩኒቲ አዳማ ካምፓስ በአንድ ግቢ የሚገኙትን ዩኒቲ ዩንቨርስቲን፣ ዪኒቲ አካዳሚን፣ ዩኒቲ የርቀት ትምህርት ክፍሎችን አስተባብሮ መምራትና ማሳደግ ሲሆን በአዲስ እንዲከፈት የተወሰነውን ዩኒቲ ቴክኒክና ሙያ ፕሮግራም ተከፍቶ ሥራ የሚጀምርበት ሁኔታ በበላይነት መምራትና ማሳለጥ ነበር። በዩኒቲ ዩንቨርስቲ 7 ወራት ቆይታው ብዙ ለውጦችን ያስመዘገበ ሲሆን ተቋሙ ያለበትን ሁለንተናዊ ችግር አንድ በማጥናት በተለይ የትምህርት ጥራት ችግርን መሠረት በማድረግ ለ13 የዩንቨርስቲው መምህራን፣ ለ34 የአካዳሚው መምህራን፣ እንዲሁም ዩንቨርስቲው በኮሙኒቲ ሰርቪስ ፕሮግራሙ በያዘው ዕቅድ መሠረት ለ14 የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በማስተማር ዘዴና በስነማስተማር ሳይንስ፣ በሥርዓተ ትምህርት ልማት፣ በኢዱኬሽናል ሳይኮሎጂ፣ በአካታች የማስተማር ጥበብ፣ በቻይልድ ሳይኮሎጂ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀመ፣ ወዘተ ስልጠና የሰጠ ሲሆን አስፈላጊ የስልጠና ማቴሪያሎችን ሰርቶ ለሰልጣኞችና ለየክፍሎቻቸው አድሏል። በተጨማሪ በግቢውስጥ በሁሉም ሰክሽኖች ውስጥ የነበሩ አያሌ ተግዳሮቶች በጥናት ተለይተው ተቀርፈዋል።
13. የዶ/ር ጥላሁን ከዩኒቲ ዩንቨርስቲ በክብር መሸኘት
ዶ/ር ጥላሁን በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳድረው ካሸነፉ በኋላ ለከፍተኛ አገራዊ ተልዕኮ ለመዘጋጀት በማሰብ የሚወዱትንና ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፍላቸውን ዩንቨርስቲ መልቀቅ እንዳለባቸው ከውሳኔ በመድረስ ከተቋሙ ጋር በገቡት ውል መሠረት የአንድ ወር ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ተቋሙን ለቀው ወጥተዋል።
ይህ ለእናት አገር ኢትዮጵያ ሲባል የተከፈለ መስዋዕትነት ነው ማለት ይቻላል።
14. የዶ/ር ጥላሁን የፖለቲካ ተሳትፎ
የዶ/ር ጥላሁን ኤርዱኖ ፖለቲካዊ ተሳትፎ የተጠናከረው ኮሌጅ ቢሆንም አገሪቱ የነበረችበት የፖለቲካ ቀውስ የበለጠ የተረዳው የ2ኛ ደረጃ መምህር እያለ ከ1976 - 1978 በነበረው ጊዜ ሲሆን፣ ይህውም ህወኃትና ሻዕቢያ የሱዳንና የግብጽን ርዳታ ተደግፈው ኢትዮጵያን በሚዋጉበት አካባቢ በማስተማር ሥራ ላይ ስለነበር በየቀኑ ኮረም ከተማ የሚገባው ቁስለኛና ሙት ያስተውል ስለነበር ነው። በተረፈ አገሩን ከየትኛውም ጽንፈኛ ከመከላከል ውጭ በፓርቲ የታቀፈበት ሁኔታ አልነበረም።
ዶ/ር ጥላሁን በፓርቲ ተመዝግቦ ለመታገል በከፍተኛ ደረጃ ፍላጎት የነበረው 2ኛ ዲግሪውን ጨርሶ እንደመጣ በ1984 ዓ/ም ቢሆንም የዚያን ወቅት ፓርቲዎች ዘርን እንጅ የፖለቲካ አይድዮሎጂ መሠረት ያደረጉ ባለመሆናቸው ዳር ሆኖ ማየቱን ቀጠለ።
በፓርቲ ታቅፎ የፖለቲካ ትግል ማድረግ የጀመረው በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ኢዜማን ወክሎ ለህ/ተ/ም/ቤት እንዲወዳደር በቀረበለት ጥሪ መሠረት ነበር። በዚያ ምርጫ እጅግ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጎ እንደሚያሸንፍ በመረጋገጡ በሚያሳዝን ሁኔታ ምንም ምክንያት ሳይኖር ምርጫው ለ3 ጊዜ እንዲቀየር ተደረገ። የዛሬ 5 ዓመት ያጣው ዕድል በሰባተኛው አገኘው።
ከዚህ በተረፈ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ካስፈለገ CVውን መመልከት ይቻላል።