ምክር ቤቱ በአንቀጽ 55፣ አንቀጽ 70(1)፣ አንቀጽ 79(4)(ሐ)፣ አንቀጽ 82(2)(ሐ)፣ አንቀጽ 101፣ አንቀጽ 102፣ አንቀጽ 103 እና... የተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል።
የሕይወት ታሪክ
የሕይወት ታሪክ
ዶ/ር ገመቹ አራርሳ ረጋሳ (PhD) በከፍተኛ ትምህርት፣ በመንግሥት ተቋማትና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ከ20 ዓመታት በላይ የሙያ፣ የአመራርና የተግባር ልምድ ያካበቱ ምሁር፣ ተመራማሪ፣ የሥራ አመራር አማካሪና የተቋም አመራር ናቸው። በረጅም የሥራ ዘመናቸውም በአሰልጣኝነት፣ በምርምር ስራ፣ በማማከርና በተለያዩ የአመራር ኃላፊነቶች አገልግለዋል።
ዶ/ር ገመቹ ጠንካራ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥራ አመራርና በሕዝብ አስተዳደር የባችለር ዲግሪ (B.A.) እንዲሁም በሕዝብ አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪ (MPA) አግኝተዋል። በተጨማሪም በሕዝብ አስተዳደር የዶክትሬት (PhD) ዲግሪያቸውን በሕንድ ከሚገኘው ፓንጃብ ዩኒቨርሲቲ (Panjab University) አግኝተዋል። የዶክትሬት ጥናታቸውም በኢትዮጵያ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ የሰው ሃብት አመራር ሥርዓት ላይ ያተኮረ ነበር።
ዶ/ር ገመቹ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ሠርተዋል። በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ እስከ ሌክቸረርነት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እስከ ረዳት ፕሮፌሰርነት ደረጃ ድረስ አገልግለዋል። በተጨማሪም በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል በተቋሙ አመራርና ልማት ላይ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው 6ኛው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) አባል ሆነው ተመርጠዋል። ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በጨፌ ኦሮሚያ የመንግሥት በጀትና ሀብት ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው አገልግለዋል። በዚህ ኃላፊነታቸው የአስፈጻሚ አካላትን ዕቅድና የሥራ አፈጻጸም በመከታተል፣ በመንግሥት ፖሊሲና ሕጎች አወጣጥና አተገባበር ሂደት ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ፣ የመንግሥት በጀትና የገቢ አስተዳደር ሥርዓትን በመከታተል እንዲሁም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን አፈጻጸም በመገምገም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃትና በታማኝነት ተወጥተዋል።
ዶ/ር ገመቹ በሙያና በአመራር ዘርፎች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች የተገነባ ሰፊ የሥራ ልምድ ያላቸው ሲሆን፣ ባገለገሉባቸው ተቋማት የተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ የለውጥ ሂደትና የሥራ አፈጻጸም ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በተለይም በስትራቴጂክ አመራር፣ በመንግሥት ፖሊሲና አስተዳደር፣ በሰው ኃይል አመራር፣ በተቋማዊ ለውጥና ልማት እንዲሁም በሌሎች ተዛማጅ ዘርፎች ላይ በርካታ የምርምርና የጥናት ሥራዎችን አከናውነዋል። በእነዚህ ዘርፎች የማማከርና የሙያዊ ሥልጠና አገልግሎት በመስጠትም በአመራር አቅም ግንባታና በተቋማዊ ሽግግር ሂደት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ዶ/ር ገመቹ በትምህርትና በሥራ ዓለም ያካበቱትን እውቀት፣ ልምድና ሙያዊ ብቃት ለሌሎች ለማጋራት በሳይንሳዊ ህትመቶች፣ በጥናትና በምርምር ጉባኤዎች፣ በህትመትና በብሮድካስት ሚዲያዎች እንዲሁም በሌሎች ተዛማጅ መድረኮች ላይ በመሳተፍ ሙያዊ ሐሳቦቻቸውን በስፋት ያካፍላሉ። በዚህም በአመራር፣ በሕዝብ አስተዳደርና በተቋማዊ ልማት ዘርፎች አዎንታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ።
ስለ ዶ/ር ገመቹ አራርሳ ረጋሳ የትምህርት ዝግጅት፣ የሙያ ልምድ፣ የአመራር ኃላፊነቶች፣ የምርምር ሥራዎችና ህትመቶች እንዲሁም ሌሎች ሙያዊ አስተዋጽኦዎች ዝርዝር መረጃ በCurriculum Vitae (CV) ውስጥ በስፋት ቀርቧል።