የሕይወት ታሪክ

እኔ የሺመቤት ደምሴ ሰዋገኝ (ዶ/ር) ከእናቴ ወይዘሮ ብርቅነሽ ሰውነት እና ከአባቴ አቶ ደምሴ ሰዋገኝ ሀምሌ 29 ቀን 1968 ዓ.ም በታሪካዊቷ ደብረ ማርቆስ ከተማ ተወለድኩ። እድሚዬ ለትትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በደብረ ማርቆስ ከተማ እና በባሶ ሊበን ወረዳ የጁቤ ከተማ ተከታተልኩ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በደብረ ዘይት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀቅሁ። ለከፍተኛ ትምህርት የነበረኝን ፍላጎትና ትጋት በመቀጠል የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪዬን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አገኘሁ። የትምህርት ጉዞዬን የበለጠ በማስፋትም የሦስተኛ ዲግሪዬን (PhD) በህንድ ሀገር ከሚገኘው ታዋቂው አንድህራ ዩኒቨርሲቲ (Andhra University) በጥሩ ውጤት አጠናቅቄ ተመረቅሁ። የስራ ልምድና ሙያዊ አገልግሎት በትምህርትና በአመራር ዘርፍ ረጅም ዓመታትን በቅንነትና በትጋት አገልግያለሁ። የስራ ህይወቴ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲ) በመምህርነት የተጀመረ ሲሆን፣ በትምህርት ማህበረሰቡ ውስጥ በርካታ ዜጎችን ኮትኩቼ አፍርቻለሁ። በተጨማሪም በተለያየ የአመራር እርከን ላይ በመስራት፣ በክልል ቢሮ በምክትል ኃላፊነት፣ በዋና ኦዲተርነት እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ በፓርላማ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ሀገሬንና ህዝቤን በግንባር ቀደምትነት በማገልገል ላይ እገኛለሁ። የቤተሰብ ህይወት በተመለከተ ከባለቤቴ ከእቶ ቆያቸው አያሌው ጋር በትዳር ተጣዝምደን 4 ወንዶች ልጆችን አፍርተናል። ነገር ግን፣ በ2012 ዓ.ም ውድ ባለቤቴን በሞት በማጣቴ ምክንያት ከፍተኛ ሀዘን ቢገጥመኝም፣ ጠንካራ እናት በመሆን ልጆቼን በብቸኝነት፣ በፍቅርና በተገቢው እንክብካቤ እያሳደግሁ እገኛለሁ። በአጠቃላይ የህይወት ጉዞዬ በትምህርት፣ በሀገር አገልግሎት፣ በጽናትና ለቤተሰብ በሚሰጥ ጥልቅ ፍቅር የተሞላ ሲሆን፤ አሁንም ሀገሬንና ልጆቼን በሙሉ ጥረት ማገልገሌን ቀጥያለሁ።