የሕይወት ታሪክ

የህይወት ታሪኬ በአጭሩ ዶ/ር ኤቢሳ ዳባ ሙለታ እባላለሁ። የተወለድኩት ታህሳስ 28/1973 ዓ.ም ከአባቴ ቄስ ዳባ ሙለታ ገመዳ እና ከእናቴ ከአለሚ ጉያሳ ዋቅዋያ በምስራቅ ወለጋ ዞን ሲሬ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ከ1979 እስከ 1986 ዓ/ም ድረስ በሲሬ የመጀመሪያ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል፣ እንዲሁም ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በሲሬ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1987 እስከ 1990 ዓ/ም ድረስ ተምሬያለሁ። ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ የሚያበቃ ውጤት በማምጣቴ፣ በ1992 ዓ/ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በውጭ ቋንቋዎች እና ስነ-ጽሑፍ የባችለር ዲግሪ ትምህርቴን የተከታተልኩ ሲሆን፣ ሰኔ 1996 ዓ/ም በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቄያለሁ። ከምረቃዬ በኋላ፣ በአምቦ በሚገኘው ሞጎር መምህራን ኮሌጅ (Mogor Teachers’ College) በተባለ የግል ኮሌጅ ተቀጥሬ ለሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ያህል አስተምሬያለሁ። በ1999 ዓ/ም ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሲቋቋም የማስተማር፣ የአስተዳደር እና የማደራጀት ሥራዎችን ከጀመሩት ቀዳሚ ተቀጣሪዎች አንዱ ነኝ። በታህሳስ 1 ቀን 1999 ዓ/ም የቋንቋዎች ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆኜ የተሾምኩ ሲሆን፣ እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2000 ዓ/ም ድረስም አገልግያለሁ። ከአንድ ዓመት በኋላ፣ ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛው የትምህርት መርሃ ግብር በተጨማሪ የተከታታይ ትምህርት መርሃ ግብር ሲጀምር፣ እኔም ከጥቅምት 14 ቀን 2000 እስከ መስከረም 2001 ድረስ የዚሁ መርሃ ግብር አስተባባሪ ሆኜ ተመድቤ ሠርቻለሁ። በበ2001 የማስተርስ ዲግሪ ትምህርቴን እንግሊዝኛ ቋንቋን እንደ ዉጭ ቋንቋ የማስተማር (TEFL) ለመከታተል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመከታተል በሰኔ 2002 ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ትምህርቴን አጠናቅቄያለሁ። ወደ ሥራ ከተመለስኩ በኋላ፣ በቋንቋዎች ጥናትና ጋዜጠኝነት ኢንስቲትዩት (Institute of Language Studies and Journalism) በሬጂስትራር ኃላፊነት ተመድቤ ከነሐሴ 9/2002 እስከ መስከረም 8/2003 ድረስ አገልግያለሁ። ከአንድ ዓመት በኋላ፣ የዚሁ ኢንስቲትዩት ዲን በመሆን ያገለገልኩ ሲሆን፣ ከመስከረም 8፣ 2003 እስከ ሐምሌ 02፣ 2003 ድረስ በዚያው ሠርቻለሁ። በአዲስ የአደረጃጀት ለውጥ ምክንያት፣ የማህበራዊ ሳይንስና ትምህርት ኮሌጅ (College of Social Science and Education) የትምህርት አግባብነትና ጥራት ጽሕፈት ቤትን በማደራጀትና በዳሬክተርነት ተመድቤ፤ ለዶክትሬት (PhD) ትምህርቴ እስክሄድ ድረስም (ከሐምሌ 02/2003 እስከ መስከረም 11/2006) ለዓመት ተኩል ያህል በዚያ ኃላፊነት ላይ አገልግያለሁ። በዚያው ዓመት፣ ጥቅምት 2007 ዓ/ም ለፒኤችዲ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀልኩ። ያለመታከት በሙሉ ቁርጠኝነት ሰርቼ በታህሳስ 14/2012 ዓ/ም የ3ኛ ድግሪ ትምህርቴን አጠናቅቄያለሁ። ወደ መደበኛ ሥራዬ፣ የማስተማር ሙያዬ ስመለስ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራር ከጥቅምት 20/2013 ዓ/ም ጀምሮ ጳጉሜ 4/2018 ድረስ የዩኒቨርሲቲውን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ቢሮ ላይ በዳይሬክተርነት ሲሰራ ቆይቻለሁ። በ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ በምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ኦሮሚያ ክልል በሲቡ ሲሬ የምርጫ ክልል የብልጽግና ፖርቲን በመወከል ተወዳድሬ ፓርቲዬ ስለተመረጠ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን ተመርጫለሁ። በሥራ ዘመኔ፣ በማስተማርም ሆነ በአካዳሚክ አስተዳደር ኃላፊነቶች፣ በአያሌ የቋሚ እና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ውስጥ እንደ ሰብሳቢ እና አባል ሆኜ አገልግያለሁ። አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል፡- 1. የቋሚ ኮሚቴ ከሚያዚያ 2017 ጀምሮ በዩኒቨርሲቲዉ አስተዳደር ቦርድ ስር የወለጋ ዩኒቨርሲቲ-ባለድርሻ አካላት ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባል፣ የሴኔት አባልና የሴኔት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የዎለጋ ዩኒቨርሲቲ የእንፎ ሳይንስና ጪጮ ኒዉስሌተሮች የአርትዖት ኮሚቴ አባል፤ የተማሪዎች ምርቃትና መጽሔት ኮሚቴ አስተባባሪ፤  የአካዳሚክ ሰራተኞች ቅጥር ኮሚቴ አባል፤ የስኮላርሺፕ ኮሚቴ አባል፤ ወዘተ በመሆን ሠርቻለሁ። 2.በጊዜያዊ ኮሚቴ አስተባባሪነትና አባልነት በብዙ ጊዜያዊ የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ውስጥ እንደ አስተባባሪ እንዲሁም አባል ሆኜ ሠርቻለሁ፤ ለምሳሌ፡ የምረቃ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የሀገር-አቀፍና እና ዓለምአቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ-የተቋማዊ ፕሮፋይል አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ-ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ጽ/ቤት የማቋቋሚያ ሰነድ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል፣ የወዩ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP) አዘጋጅ ኮሚቴ አባል፣ የሪፖርቶች እና የፕላን ዝግጅት ኮሚቴ አባል፣ እንዲሁም በርካታ ተጨማሪ በዩኒቨርሲቲ እና ሀገርአቀፍ ጀረጃ የፓናል ውይይቶችን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምሁራን መድረክን፣ የሰላም ኮንፈረንስን እና በመሳሰሉት ኮሚቴዎች ሰርቻለሁ። በጥቅምት 2001 ዓ/ም ከወ/ሮ መስከረም ነጋሳ ያሊ ጋር ትዳር በመመሥረት እና ዋዳ፣ ሞኤራ፣ ሂካ እና ሳሙኤል በሚባሉ በአራት ቆንጆ ልጆች እግዚአብሔር ባርኮናል።