የሕይወት ታሪክ

ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ ፈይሳ ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ ፈይሳ በማህፀንና ፅንስ ጤና ሕክምና ስፔሻሊስት ሐኪም ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ሆነው ያገለግላሉ። ዶ/ር መቅደስ የሕክምና ትምህርታቸውን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው የሕክምና ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማህፀንና ፅንስ ጤና ሕክምና ስፔሻላይዜሽናቸውን አጠናቀዋል። በተጨማሪም በቤተሰብ ዕቅድ ሕክምና ልዩ የሙያ ሥልጠና በመከታተል በዚህ ዘርፍ የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ሱብ-ስፔሻሊስት ሆነዋል። ከሚኒስትርነት ኃላፊነታቸው በፊት ዶ/ር መቅደስ በተለያዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት በሕክምና፣ በሕዝብ ጤና፣ በአካዳሚክ እና በጤና ሥርዓት ልማት ዘርፎች ሰፊ ልምድ አካብተዋል። በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ዋና መሥሪያ ቤት በጄኔቫ የቡድን መሪና የሕክምና/ቴክኒክ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል። እንዲሁም የCenter for International Reproductive Health Training (CIRHT) የአፍሪካ ቢሮ ዳይሬክተር፣ የCollege of Obstetricians and Gynaecologists of East, Central and Southern Africa (COECSA) የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ፣ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ክፍል ሀላፊ እና የማህፀንና የፅንስ ጤና ሕክምና ክፍል ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። በሙያ ማኅበራት ዘርፍም ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የማህፀንና የሴቶች ሐኪሞች ማኅበር (ESOG) ጸሐፊ እና በኋላም ፕሬዝዳንት ሆነው መርተዋል። በተጨማሪም በWHO የአፍሪካ ክልላዊ ጽሕፈት ቤት የእናቶች፣ የሕፃናትና የወጣቶች ጤና ቴክኒካል አማካሪ ቡድን አባል ሆነው አገልግለዋል። ዶ/ር መቅደስ በሴቶች ጤናና በሕዝብ ጤና ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋፅኦ በርካታ አገራዊና ዓለም አቀፍ እውቅናዎችን አግኝተዋል። በተለይም የዓለም አቀፉ የማህፀንና የሴቶች ሕክምና ፌዴሬሽን (FIGO) በ2021 የWomen’s Award እና በ2025 የDistinguished Merit Award በመስጠት ለሴቶች ጤና ላበረከቱት ልዩ አስተዋፅኦ እውቅና ሰጥቷል። በጤና ሚኒስትርነታቸው፣ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ፈይሳ የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ይበልጥ ዘላቂ፣ ተደራሽ፣ በአገራዊ አቅም የተመሠረተ እና ለተለያዩ የጤና ቀውሶች በተሻለ ሁኔታ ምላሽ መስጠት የሚችል ለማድረግ በበርካታ ቁልፍ የሥራ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት አድርገዋል። ከእነዚህም መካከል ዘላቂ የጤና ፋይናንስን ማጠናከር፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎትን ማጠናከርና ማዘመን፣ የዲጂታል ጤና ሽግግርን ማፋጠን፣ የመድኃኒትና የጤና ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ማምረትን ማስፋፋት እና የአገር ባለቤትነትን የሚያጠናክሩ አገር መር አካሄዶችን ማስፋፋት ይገኙበታል። ዶ/ር መቅደስ በተለያዩ ብሔራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት የአመራርና የቦርድ ኃላፊነቶችን በመወጣት ላይ ይገኛሉ። የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ShieldVax፣ Gavi, the Vaccine Alliance እና የpandemic fund የቦርድ አባል ናቸው። በተጨማሪም የAfrica Centres for Disease Control and Prevention (Africa CDC) የአስተዳደር ቦርድ ተባባሪ ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ በNational Council for the Risk and Disaster Management Commission አባልነትም ያገለግላሉ።