ምክር ቤቱ በአንቀጽ 55፣ አንቀጽ 70(1)፣ አንቀጽ 79(4)(ሐ)፣ አንቀጽ 82(2)(ሐ)፣ አንቀጽ 101፣ አንቀጽ 102፣ አንቀጽ 103 እና... የተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል።
የምርጫ ክልል
አማራ
ክልል:
አማራ
በካርታው ላይ ለማየት ጠቅ ያድርጉ
የሕይወት ታሪክ
የሉባባ ሰይድ ለጋስ የሕይወት ታሪክ
ስሜ ሉባባ ሰይድ ለጋስ ይባላል። በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ መቅደላ ወረዳ 06 ቀበሌ ግንቦት 24 ቀን 1973 ዓ.ም. ተወለድኩ። ከልጅነቴ ጀምሮ ትምህርትን እንደ የሕይወቴ መሠረት በመቁጠር ለመማርና ራሴን ለማሻሻል በትጋት ሠርቻለሁ።
የትምህርት ሕይወቴ
የ1ኛ ደረጃ ትምህርቴን በመቅደላ ወረዳ ማሻ ከተማ ጀምሬ ተምሬያለሁ። ከዚያም የ2ኛ ደረጃ ትምህርቴን በተንታ ወረዳ ቀጥዬ ተምሬያለሁ።
ከ2ኛ ደረጃ በኋላ በአላጌ ግብርና ኮሌጅ የሰብል ልማት ዲፕሎማዬን አግኝቻለሁ። በመቀጠል በወሎ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ተምሬ ጨርሻለሁ። የትምህርት ጉዞዬንም በመቀጠል በወሎ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የ2ኛ ዲግሪዬን አግኝቻለሁ።
ቤተሰብና የግል ሕይወት
በቤተሰብ ውስጥ አባቴና እናቴ እንዲሁም ሁለት እህቶች አሉኝ። በአሁኑ ጊዜ ባለትዳር ሲሆን የአራት ልጆች እናት ነኝ። ቤተሰቤ ለእኔ የጥንካሬ፣ የፍቅርና የመነሳሳት ምንጭ ነው።
በሕይወቴ ያጋጠሙኝ ፈተናዎች
የሕይወት ጉዞዬ ቀላል አልነበረም። ከዲፕሎማ እስከ 2ኛ ዲግሪ ድረስ ትምህርቴን እየተከታተልኩ ቤተሰብ መሥርቼ ልጆችን አሳድጌያለሁ። በዲፕሎማዬ ትምህርት ላይ እያለሁ የመጀመሪያ ወንድ ልጄን ወለድኩ። ከወለድኩ ከአንድ ወር በኋላ ወደ ትምህርት ተመለስኩ። ይህም ትምህርትን ለማቋረጥ ሳይሆን ለሕልሜ የበለጠ እንድታገል አድርጎኛል።
የመጀመሪያ ዲግሪዬን እየተማርኩ ሁለተኛ ልጄን ወለድኩ። ሦስተኛ ልጄን ከወለድኩ በኋላም የማስተርስ ትምህርት ዕድል አገኘሁ። አራተኛዋ ልጄ ደግሞ የፓርላማ አባል ሆኜ በነበርኩበት ጊዜ ተወለደች። ስለዚህ ልጆቼ በትምህርትና በሥራ ጉዞዬ አብረውኝ የተጓዙ የሕይወቴ ትልቅ ክፍል ናቸው።
በተለይም የመጀመሪያ ዲግሪዬንና ማስተርስ ትምህርቴን በምማርበት ወቅት አባቴና እናቴ ለረጅም ጊዜ ታመው ነበር። ይህ ሁኔታ በጣም አሳስቦኝና አስጨንቆኝ ነበር። ሆኖም በውስጤ “አልበገርም፤ የጀመርኩትን እጨርሳለሁ” የሚል አቋም በመያዝ ትምህርቴን በትጋት ቀጠልኩ። በመጨረሻም የጀመርኩትን ትምህርት በስኬት ጨረስኩ።
ስኬቶቼ
ከትምህርቴ በተጨማሪ ወደ ንግድ ዘርፍ በመግባት የራሴን ሥራ ለመጀመር ችያለሁ። በስሜ አፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት ገንብቼ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት መስጠት ችያለሁ። በምሠራቸው መልካም ሥራዎችም የሕዝብ ተቀባይነትና እምነት አግኝቻለሁ።
ለእኔ ስኬት ማለት የትምህርት ዲግሪ ብቻ ሳይሆን ያገኘሁትን እውቀት ለራሴ፣ ለቤተሰቤና ለማኅበረሰቡ ጥቅም ላይ ማዋል ነው። በአጠቃላይ በመንግስት የስራ ልምድ 21 አመት ያገለገልኩ ሲሆን በተለያዪ የአመራርነት ቦታዎች 15 አመት በባለሙያ 6 አመት ከዚህ ውስጥ 6 አመት የወረዳየን ህዝብ በመወከል በአማራ ክልል ምክር ቤት አባል እና የግብርና ጉዳዪች ቋሚ ኮሚቴ አባል በመሆን በመቀጠል በ6ኛው ዙር የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አባል በመሆን ለአምስት አመት እያገለገልኩ እገኛለሁ።
የወደፊት ዕቅዴ
በቀጣይ ከመንግሥት ሥራ ወጥቼ በግሌ ሥራ ላይ በመሰማራት የበለጠ ለማደግ እፈልጋለሁ። በተለይም ደረቅ እንጀራን ወደ ውጭ አገር በመላክ የኤክስፖርት ንግድ ለመጀመር ዕቅድ አለኝ። ይህንንም በማድረግ ለራሴና ለቤተሰቤ የተሻለ ሕይወት ከመፍጠር ባሻገር ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠርና ለሀገሬ ኢኮኖሚ የራሴን አስተዋጽኦ ማበርከት እፈልጋለሁ።
የሕይወቴ ታሪክ የትጋት፣ የጽናትና የተስፋ ታሪክ ነው። ትምህርትን፣ ቤተሰብንና ሥራን በአንድ ላይ ለማስኬድ ብዙ ፈተናዎችን ብጋፈጥም ተስፋ አልቆረጥኩም። ያጋጠሙኝ ችግሮች እንዳልበገር አስተምረውኛል።
ዛሬ የደረስኩበት ደረጃ በቀላሉ የተገኘ ሳይሆን በትጋት፣ በጽናት፣ በትዕግሥትና በተስፋ የተገነባ ነው። ወደፊትም ያለኝን ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም ለቤተሰቤ፣ ለማኅበረሰቤና ለሀገሬ የበለጠ ጠቃሚ ሰው ለመሆን እተጋለሁ።