በኤጀንሲዎች አማካኝነት ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን የደመወዝ ክፍያ ፍትሀዊነት ማረጋገጥ የሚያስችል ጥናት ተጠንቶ ወደ ስራ መገባት እንዳለበት ተገለጸ

(ዜና ፓርላማ) ግንቦት 02 ቀን 2013 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማህበራዊ እንዲሁም የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በተለያዩ ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ በኤጀንሲዎች አማካኝነት ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን የደመወዝ ክፍያ ፍትሀዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ጥናት በፍጥነት ተጠንቶ ወደ ስራ መገባት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በአንዳንድ የግል ኤጀንሲዎች አማካኝነት በባንኮችና በተለያዩ ኤጀንሲዎች ተቀጥረው የሚሰሩ የጥበቃና የጽዳት ሰራተኞችን መብትና ጥቅም የሚጎዱ ስራዎች እንደሚሰሩ የመስክ ምልከታ ለማድረግ በተለያዩ ተቋማት በተንቀሳቀሱበት ወቅት ተበደይ ሰራተኞች ለኮሚቴው አባላት እንዳነሱላቸው የጠቅሱት የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሰቢ የተከበሩ አበባ ዮሴፍ ናቸው፡፡

ይህንንም ችግር ለመፍታት ከሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ከአሰሪና ሰራተኛ ኮንፌዴሬሽን እንዲሁም ከተለያዩ ኤጀንሲዎች ጋር በመተባበር የሰራተኞችን የአገልግሎት ክፍያ ደመወዝ ማስጠበቅ የሚያስችል ጥናት ተጠንቶ መቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚንስትር ዴኢታ የተከበሩ  ጫኔ ሸመካ በበኩላቸው በቀጣሪ የግል ኤጀንሲዎች፣ የማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴርና በሰራተኛ ማህበራት መካከል ከሚታዩ መገፋፋቶች ወጥቶ ሁሉም አካላት ቁጭ ብለው በችግሮቻቸው ዙሪያ በመነጋገር ችግሮቻቸውን ማረምና የመፍትሄው አካልም ጭምር መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አክለውም ከሁሉም በላይ ኤጀንሲዎች የሰራተኛውን መብት ለማስጠበቅ ለወጡ ሕጎች ተገዢ እንዲሆኑም ነው በአጽንኦት የተናገሩት፡፡

በሚፍታህ ኪያር