“የተጠኑ ጥናታዊ ጽሁፎች ወደ ተግባር ገብተው የሕዝቡን ችግር እንዲፈቱ  ይደረጋል” ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ

 (ዜና ፓርላማ) ሐምሌ 04፣ 2017 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፣ የተጠኑ ጥናታዊ ጽሁፎች ወደ ተግባር ገብተው የሕዝቡን ችግር እንደሚፈቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ ገልጸዋል፡፡

ምክትል አፈ-ጉባኤዋ ይህንን ያሉት የምክር ቤቱን ጥናት እና ምርምር ኮንፈረንስ አስመልክቶ በተካሄደ የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ላይ ነው፡፡

ምክር ቤቱ፣ የተጠኑ ጥናታዊ ጽሁፎች ወደ ተግባር ገብተው የሕዝቡን ችግር እንዲፈቱ ምክር ቤቱ ሕዝባዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ነው ወ/ሮ ሎሚ ያብራሩት፡፡

በጥናት እና ምርምር የተገኙ ምክረ-ሃሳቦችን መሰረት በማድረግ ተለዋዋጭ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳች እንደሚፈቱ የገለጹት ምክትል አፈ-ጉባኤዋ፣ የተጠኑ ጥናቶች ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ጥናታዊ ጽሁፎችን ላቀረቡ እና በሂደቱ ለተሳተፉ አካላት ወ/ሮ ሎሚ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ የእውቅና መርሃ-ግብርም ተከናውኗል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽ/ቤት የአስተዳደራዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ጸሃፊ አቶ ከረዩ ባናታ በበኩላቸው፣ የጥናት እና ምርምር ስራዎች ተደራሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ እና እየዘመነ እንዲሄድ የምክር ቤቱ ጽ/ቤት ሚናውን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡