ጠንካራ ተቋም በመገንባት እና የአሠራር ሥርአት በመዘርጋት የሴቶችን ተሳትፎና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል
"ጠንካራ ተቋም በመገንባት እና የአሠራር ሥርአት በመዘርጋት የሴቶችን ተሳትፎና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል"
----- ምክትል አፈ ጉባዔ -----
(ዜና ፓርላማ) ሚያዚያ 16፣ 2017 ዓ.ም፤ ጠንካራ ተቋም በመገንባት እና የአሠራር ሥርአት በመዘርጋት የሴቶችን ተሳትፎና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ እና የሴቶች ኮከስ የበላይ ጠባቂ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ ተናግረዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴት ተመራጮች ኮከስ የሥራ አስፈፃሚ አባላት የኮከሱን የሦስት አመት ተኩል የተግባር አፈፃፀም ገምግመዋል፡፡
በዚሁ ጊዜ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ፤ ኮከሱ ባለፉት ሦስት አመት ተኩል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ የሠው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች ከተለያዩ አካላት ሃብት በማሰባሰብ 65 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የቁሳቁሶች ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነቱን በብቃት መወጣት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም የውስጥ እና የውጪ አቅምን በመጠቀም ለሴቶች ኮከስ አባላት እና ለወንድ ተባባሪ አባላት በምክር ቤቱ ዋና ዋና ተግባራት ላይ ትኩረት ያደረጉ ከ60 በላይ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች የተሠጡ ሲሆን፤ ከ2ዐ ሚሊዩን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም አመላክተዋል፡፡
እስካሁን በተሰጡ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችም የኮከስ አባላቱን ብቃት በማሳደግ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የሕግ አወጣጥ፣ የክትትልና ቁጥጥር፣ የውክልናና የፓርላማ ዲኘሎማሲ ስራዎችን በብቃት እንዲያከናውኑ ትልቅ እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ኮከሱ የመላው ሴቶች ውክልና ያለበት በመሆኑ በሀገር ደረጃ በሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ የሴቷን ተሣታፊነትና ተጠቃሚነት ታሳቢ ሊደርግ ይገባል ሲሉ ምክትል አፈ ጉባዔዋ ገልፀዋል፡፡
ለአብነትም በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ፣ በቀጣይ በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫና በሌሎች ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ፍትሀዊ ውክልና እንዲኖራቸው በማድረግ ከመቸውም ጊዜ በላይ ተሣትፎአቸውን ለማሳደግ ከወዲሁ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ኮከሱ ከምክር ቤቱ ከተሰጠው ተልዕኮ አንዱ በሆነው የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች የስርዓተ ፆታ እኩልነትን የሚያረጋገጡ ተግባራት በመንግስት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በየተቋማቱ መፈፃማቸውን የማረጋገጥ ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ እንደ ሀገር ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ኮከሱ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እና በቀጣይ የሚፈለገውን ዓይነት መሪ ለማፍራት ሴት የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን ከወዲሁ ለማብቃት በትኩረት እንደሚሰራም ምክትል አፈ ጉባዔ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ አብራርተዋል፡፡
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives