«የመንገድ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል»- አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ  

(ዜና ፓርላማ):- ሚያዚያ 20 2013 .. አዲስ አበባ፤ የኢ.... የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው ውይይት አገሪቱ ያላትን ውስን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም፣ መንገዶችን በጥራት ለመሥራት፣ የተያዙትን የመንገድ ፕሮጀክቶች በጊዜ ለማጠናቀቅና የህዝቡ ጥያቄ ለመመለስ  ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገነባ ነው የተከበሩ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ያሳሰቡት፡፡

የተከበሩ አፈ ጉባኤው ይህንን ማሳሰቢያ የሰጡት ቋሚ ኮሚቴው  ከፌዴራልና ከክልል የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና ከፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው፡፡

  

የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ አክለውም የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ችግር ስለሚታወቅ ከአጭር ጊዜ አኳያ ችግሮቹን  ለመፈታት የክልል አመራሮች ወደየክልሎቻቸው ሄደው በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር በመወያየት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የተከበሩ አፈ ጉባኤው አያይዘውም በመንገድ ፕሮጀክቶች የሚታዩትን ችግሮች ከመካከለኛ ጊዜ አኳያ ለመፍታት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እቅድ በማውጣት መስራት እንዳለበት አሳስበው፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ለቋሚ ኮሚቴው ልዩ ልዩ ድጋፎችን  እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

 የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ከከተማ ልማትና ከገንዘብ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ጋር በመነጋገር ችግሮችን መፍታት እንዳለባቸው፣ የማያሰሩ ሕጎች ለማሻሻል ረቂቅ ሕጎችን አዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ እንደሚችል፣ የካሳ ክፍያ ስታንዳርድ  ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ፣ የመንገድ ፕሮጀክቶች ዲዛይን በፕላን ኮሚሽን ሳይረጋገጥ የገንዘብ ሚኒስቴር ገንዘብ መክፈል እንደሌለበትና የመንገድ ፕሮጀክቶችን የሚከታተል በየደረጃው ያለ አመራርን ተጠያቂ በማድረግ በመካከለኛ ጊዜ የሚፈቱ ችግሮች እንደሆኑ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ አስገንዝበዋል፡፡

የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አሸናፊ ጋዕሚ በበኩላቸው የመንገድ ፕሮጀክቶችን በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው ግብረ መልስ ቢሰጥም ሊስተካከል ባለመቻሉ መድረኩ እንደተዘጋጀ ጠቁመዋል፡፡

ሰብሳቢው አያይዘውም የአገሪቱን ውስን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ አገሪቱን ችግር ውስጥ የሚያስገባት መሆኑን ጠቁመው በመንገድ ፕሮጀክቶች የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች ተናበው ካልሰሩ ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል፣ ኤጀንሲው የቅንጅት እቅድ አዘጋጅቶ ለቋሚ ኮሚቴው፤ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለፕላን ኮሚሽን ቀርቦ ከተረጋገጠ  በኋላ ፕሮጀክቶች ሥራ መጀመር እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡

አቶ አሸናፊ ጨምረውም የመንገድ ፕሮጀክቶችን የሚያጓትት የሥራ ኃላፊ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበው የሙያ ማህበራትን ማጎልበትና በመተባበር የመንገድ ፕሮጀክቶችን ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰዓዳ ከድር በበኩላቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች በአግባቡ ካልተሰሩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ስለሚፈጥሩ አሁን ባለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድም የሚተላለፍ ችግር መሆኑን ጠቁመው አዋጁንና ደንቡን መሠረት በማድረግ በቆራጥነት መሥራት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኘም በበኩላቸው ችግሩን የሚያነሱት እንደ ተቋም ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም ከፍተኛ ቀውስ የሚያስገባ በመሆኑ  በአጭር ጊዜ መፈታት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ኢንጂነር ሐብታሙ አክለውም የወሰን ማስከበር ችግር የመንገድ ፕሮጀክቶችን እያጓተተ በመሆኑ ምክር ቤቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዴት እንደሚስተናገዱ አቅጣጫ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በጋሹ ይግዛው