(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 18፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሥረኛ መደበኛ ጉባዔ፤ የሀገሪቱ የትራንስፖርት ዘርፍ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አመላከተ፡፡

ፓርላማው ይህን ያመላከተው፤ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ፤ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴርን የ10 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

በትራንስፖርቱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮች ሕዝቡን ለከፍተኛ እንግልት እና ወጪ ከማጋለጣቸው ባሻገር፤ ለመልካም አስተዳደር እጦት መንስዔ እንደሆኑ ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው አንስቷል፡፡

ከፍትሐዊ የመንገድ ዝርጋታ ተደራሽነት እና ከሀገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ሁኔታ ጋር በተገናኘ፤ ለሕዝብ ምቹ ያልሆኑ፣ የሰውን ሕይወት ለአደጋ የሚያጋልጡ ክስተቶች ስለመኖራቸው፤ ምክር ቤቱ ሳይጠቁም አላለፈም፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ-ልማት እና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአዲስ መልክ መዋቀሩን እና የሠራተኞች ድልድል መካሄዱን፣ ሥራዎች በዲጂታላይዜሽን ሥርዓት ወደ አንድ ማዕከል መሰባሰባቸውን አድንቀዋል፡፡ ተቋሙ በሁሉም ዘርፎች አፈጻጸሙ የተሻለ እንደሆነም መስክረዋል፡፡

በአንጻሩ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ፣ የመናኸሪያ አገልግሎትን ለማዘመን እንዲሁም የአሽከርካሪዎች ሥነ-ምግብር እና ሕገ-ወጥ ተግባራትን አስመልክቶ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ችግሮችን በዘላቂነት እንዲፈታ፤ የተከበሩ ወይዘሮ ሸዊት አሳስበዋል፡፡

ከውጭ ሀገራት ተገዝተው የሚመጡት የተለያዩ ምርቶች እና ሸቀጦች ወደብ ላይ ለረጅም ጊዜ መቆየት እንደሌለባቸው፤ ሰብሳቢዋ አስገንዝበዋል፡፡ በሌላ በኩልም እንደ ዐይን ብሌን የምንሳሳለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ልዩ ድጋፍ እና ክትትል ሊደረግለት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ክብርት ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ ለተቋማዊ እና ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት በርካታ ሥራዎች እንደተሠሩ ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም፤ የተቋሙ የቀጣይ 30 ዓመታት የትራንስፖርት ማስተር ፕላን ዝግጅት መጨረሻ ምዕራፍ መድረሱ፣ ራሱን የቻለ ስኬት ነው ብለዋል፡፡

በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በቅርቡ የሚጸድቁ አዋጆች ዓይነተኛ መፍትሔ የሚሰጡ እንደሆነ ሚኒስትሯ ተስፋ ሰንቀዋል፡፡ የአዲስ አበባን የሕዝብ ትራንስፖርት ችግር ለማስታገሥ ለመንግስት ሠራተኞች የተመደቡ ፐብሊክ ሰርቪስ መኪኖች፤ በትርፍ ጊዜያቸው በድጋፍ ሰጪነት እንዲሠሩ መደረጉንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡ የተጨማሪ 1 መቶ 10 አውቶቢሶች ግዢም በሂደት እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩልም፤ ለትራንስፖርት ዘርፉ ፈር ቀዳጅ የሆነ እና የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኮሬንቲ ኃይል መስጫ ማዕከል (Electric Vehicles Charging Center)፤ እንዲሁም ሞዴል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ በይፋ ሥራ ማስጀመር እንደተቻለም፤ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

ከውጭ ሀገራት ተገዝተው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡትን የሎጀስቲክስ ጭነቶች፤ ጊዜ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ በተፈለጉበት ቦታዎች ለማድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የገለጹት ክብርት ወይዘሮ ዳግማዊት፤ ደረቅ ወደቦችን እንደ መጋዘን ቆጥረው ንብረታቸውን በ15 ቀን ውስጥ በማያነሱ ባለሀብቶች ርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የትራንስፖት ትስስሩን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በማቀናጀት እና ዘመናዊ በማድረግ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ገበያ ተደራሽ እንድትሆን አልመው እየሠሩ መሆናቸውን ሚኒስትሯ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ