6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን የለውጥ  ስራዎች መሰራታቸው ተገለጸ

(ዜና ፓርላማ ) ፣ ሚያዝያ 25 ፣ 2013 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፣ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን በርካታ የለውጥ ስራዎች መከናወናቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ ገለጹ ፡፡

አፈ-ጉባኤው ይህንን የገለጹት የስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ  ቅድመ-ዝግጅት አስመልከቶ ከአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢዎች ጋር በጽ/ቤታቸው በተወያዩበት ወቅት ነው ፡፡

ምርጫው ነጻ፣ፍትሃዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሳተፉበት መንገድ የምርጫ ሕጉ መሻሻሉንና  የምርጫ ቦርድ አባላት  መመረጣቸውን   ለታዛቢዎቹ አብራርተውላቸዋል ፡፡

ምርጫው በተቀመጠለት የጊዜ መርሃ-ግብር እንዲከናወን ለማድረግ የምርጫ ቁሳቁሶች ወደየምርጫ ጣቢያዎች እንደተጓጓዙ የጠቀሱት አፈ-ጉባኤው ፣ በምርጫው ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ሕጋዊ አሰራሮችና የጸጥታ አደረጃጀቶች እንደተዘረጉም ነው  የተናገሩት ፡፡

በጸጥታ ጉዳይ በአንዳንድ የሀገሪቷ አካባቢዎች ተራዝሞ የነበረው የመራጮች ምዝገባም በአሁኑ ጊዜ ከሞላ ጎደል መጠናቀቁን  የተናገሩት  አፈ-ጉባኤ ታገሠ ፤ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ታዛቢ ቡድኑ በቂ መረጃ ማግኘቱን አፈ-ጉባኤው አረጋግጠዋል ፡፡

በምርጫው የሴቶችን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግና ሴቶች መራጭ ብቻ ሳይሆኑ ተመራጭም እንዲሆኑም መንግስት በትኩረት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የጠቆሙት  አቶ ታገሠ ፣ በአሁኑ ጊዜ በአመራር ሰጭነት  የሴቶች ተሳትፎ 50 በመቶ መሆኑንም አስረድተዋል ፡፡