ምክር ቤቱ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና ሌሎች የዘርፍ ኮሚሽኖች የቀረበለትን ሹመት አጸደቀ

(ዜና ፓርላማ)፣ ሰኔ 18 ቀን 2013ዓ.ም. አምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛ አመት የስራ ዘመን ሶስተኛ ልዩ ስብሰባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እጩ ም/ዋና ኮሚሽነር እና ሶስት የዘርፍ ኮሚሽነሮችን ሹመት ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አፀደቀ

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የውሳኔ ሃሳብ ሪፖርት ለምክር ቤት አቅርበው፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ም/ዋና ኮሚሽነርን ጨምሮ ሶስት የዘር ኮሚሽነሮችን ለመምረጥ የሚያስችል የመመዘኛ መስፈርትን አሟልተው ለተገኙ እጩዎች  በአቅራቢ ኮሚቴው በኩል በግልጽ ለህዝብ የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቶ 253 ሚደርሱ ተወዳዳሪዎች ተመዝግበው  አራቱ እጩዎች መስፈርቱን አሟልተው መገኘታቸውን አብራርተዋል፡፡

በዚሁ መሰረት በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሰብዓዊ መብቶች ጥናት ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከባለሙያነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ደረጃ አመራርና አማካሪነት ሲያገለግሉ የቆዩትን ወ/ሮ ራኬብ መለሰን በም/ዋና ኮሚሽነርነት፤ በህግ የጀመሪያ ድግሪ፣ በሰብዓዊ መብቶች ጥናት ሁለተኛ ድግሪ እንዲሁም በአሁን ወቅት ዶክተሬት ዲግሪ በማጠናቀቅ ላይ የሚገኙትን ወ/ሪት መስከረም ገስጥን በሴቶችና ህጻናት መብት ጉዳይ ኮሚሽነርነት፤ በህግ የመጀመሪያ ድግሪ በማህበራዊ ስራ ዘርፍ ሁለተኛ ድግሪ ያላቸው  በተለያዩ አካል ጉዳተኞች መብቶች ስራ ውስጥ በአማካሪነት ሲሰሩ የነበሩ ወ/ሮ ርግበ ገብረሃዋሪያን በአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን መብት ጉዳይ ኮሚሽነርነት በአራተኛም በህግ የመጀመሪያ ድግሪ በሰብዓዊ መብቶች ጥናት ሁለተኛ ድግሪ እንዲሁም ዶክተሬት ዲግሪ ያለቸው አብዲ ጂብሪልን በሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ጉዳይ ኮሚሽነርነት የቀረቡትን እጩ ተሿሚዎች ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ  አጽድቋል፡፡

ሃሳባቸውን የሰጡ የምክር ቤት አባላትም የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ትኩረትን የሚሻ በመሆኑ ሃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በልዩ ስብሰባው የኢ.ፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር  እንዲሁም ጽ/ቤቱን ለማሻሻል ለየወጣውን ረቂቅ አዋጅ ለህግ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል፡፡

ረቂቅ አዋጁም ፌዴሬሽን ምክር ቤት በ1993 በወጣው አዋጅ ቁጥር 2051 መሰረት ህገ መንግስቱን የመተርጎም፣ የብሔር፣ ብሔረሰቦችን እና ህዝቦችን የወሰን፣ የእኩልነት መብት እና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲኖርና እንዲዳብር በማድረግ፣ በክልሎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን የመፍታት፣ ፍትሐዊ ድጎማ እና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል እንዲኖር በማድረግ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ሊወጣላቸው የሚገቡ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር አስፈላጊ የሆኑ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን በመለየት እንዲሁም ህገ መንግስቱን አደጋ ላይ የጣለ ክልል ካለ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ የማድረግ ስራ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰው፡፡

አዋጁ ከተቋቋመ ሁለት አስርት አመታት ያለፈበትና አገሪቱ ከያዘችው ለውጥ ጎዳና እንዲሁም አሁን እየቀረበው ካለው የህዝብ ፍላጎት ጋር ሊጣጣም ባመለቻሉ አልፎም ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱ የተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነትን በቀልጣፋ እና በውጤታማነት አለመፈጸም ብቻም ሳይሆን ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል ቁመና ላይ አለመሆኑ እና ፈርጀ ብዙ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ አዋጁ እንደገና እንዲሻሻል ካደረጉት ዋና ዋና ጉዳዮች መሆናቸውን አፈ-ጉባዔው አብራርተዋል፡፡

 በወቅቱም አባላትም ሃሳባቸውን የሰጡ ሲሆን አዋጁ አሁን ላይ መቅረቡ ተገቢ መሆኑንና ቀደም ሲል ፌዴሬሽን ምክር ቤት በተሰጠው ተልዕኮ ችግሮችን በወቅቱ ባለመፍታቱ የተነሳ በርካታ ችግሮች በየቦታው ሲከማቹ መቆየታቸውን፤ የአፈጻጸም ጉድለትም እንደነበረበት አንስተው በተለይ በክልሎች አከባቢ ከህዝብ ውክልና ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው ብለዋል፡፡ የሚሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ሁሉንም ህብረተሰብ ያሳተፈ የዲሞክራሲ ስርአትን የተከተለ እንዲሆን   የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ በእንክሮ እንድመለከተው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

በእያሱ ማቴዎስ