የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ተቋም መገንባት እንዳለበት    ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

(ዜና ፓርላማ)፣ ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ.ም፤ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዮች ቋሚ ኮሚቴ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ተቋም መገንባት እንዳለበት አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያሳሰበው ዛሬ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንን የ2013 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ የአፈጻጻም ሪፓርት በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

በግምገማውም ባለስልጣን መ/ቤቱ ከምንጊዜውም በላይ በብሮድካስት፣ በበይነ-መረብ፣ እንዲሁም በህትመት ውጤቶች የሚተላለፉ ዜናዎችን ከመቆጣጠርና የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ ከማድረግ አኳያ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባላስልጣን የሀገሪቱን አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን መሰረት ያደረገ ጠንካራና ገለልተኛ እንዲሁም የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት የሚያስጠብቅ ተቋም ሆኖ መገንባት እንዳለበትም ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል፡፡

ተቋሙ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት የሚጎዱ የውስጥና የውጪ የሚዲያ ስጋቶችን ቀድሞ መተንተን በሚያስችል እና ሙያውን በባለቤትነት ስሜት ተቀብሎ ሀያ አራት ሰዓት በንቃት በሚከታተል የሰው ኃይል መገንባት እንዳለበትም ነው ቋሚ ኮሚቴው ያስገነዘበው፡፡     

ቋሚ ኮሚቴው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በበጀት አመቱ ካከናወናቸው አበይት ተግባራት ውስጥም የፍቃድና የምዝገባ አገልግሎትን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ማቅረብ መቻሉን፣ ከሃምሳ አንድ በላይ ለሚሆኑ የፊልምና የዶክመንታሪ ዝግጅቶች ፍቃድ መስጠት መቻሉን በዋናነት በጠንካራ አፈጻፀም አንስቷል፡፡

መጪውን ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በተመለከተ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ነጻ የአየር ጊዜና የጋዜጦች አምዶችን በመመደብ እና ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጋር ተቀናጅቶ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቱም ሌላው በቋሚ ኮሚቴው  በጠንካራ አፈፃጸም የተነሳ ነው፡፡

በሚፍታህ ኪያር