(ዜና ፓርላማ) ጥር 5 2017 .ም፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ከዴንማርኳ ልዕልት ቤኔዲክቴ አስትሪድ ጋር በኢትዮጵያ እና በዴንማርክ መካከል ስለሚኖረው የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ተወያይተዋል፡፡

በዴንማርኳ ልዕልት ቤኔዲክቴ አስትሪድ ኢንጌቦርግ የተመራው የልኡካን ቡድን በዛሬው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉብኝት በማድረግ ከአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ቀደም ሲል የነበራቸውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት በማጠናከር በተለያዩ ዘርፎች አብሮ ለመስራት ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም እንዳላት የተከበሩ አቶ ታገሰ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ አካታች የሆነ ሀገራዊ ምክክር በማካሄድ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ስለመሆኑም አፈ ጉባኤው ለልኡካን ቡድኑ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ለትምህርት በተለይም ለሴቶች እና ህጻናት እንዲሁም ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ስለመሆኑም የተከበሩ አቶ ታገሰ አብራርተዋል፡፡

ልዕልት ቤኔዲክቴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች እየሰራችው ያለውን ስራ የዴንማርክ መንግሥት ማገዝ እንደሚፈልግ አስታውቀዋል።

( አበባው ዮሴፍ)