በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ በመሥራቱ፣ ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ማገልገል መጀመሩን ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የኮሚሽኑን የአሥር ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባዳመጠበት ወቅት፤ ኮሚሽኑ በሀገር ውስጥ ላሉ የዴሞክራሲ ተቋማት እና ለሌሎች ሀገራት ጭምር ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን እንደተረዳ ገልጿል፡፡ ይህንንም ተሞክሮውን ለማስፋት ከሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንዳለበትም አሳስቧል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ፤ ኮሚሽኑ በአዋጅ የተቋቋመበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ ከመሥራቱም ባሻገር፣ ሰብዓዊ መብቶች በዘላቂነት እንዲከበሩ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ስለተመለከተው፤ ይህንን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ሰብሳቢዋ አክለውም፤ በሰዎች ላይ የሚከሰተውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመከላከል ተቋማት ነፃ ሆነው የመሥራት መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ኮሚሽኑ ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከማረሚያ ቤቶች፣ ከፍርድ ቤቶች እና ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ቢሠራ የበለጠ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ተማሪዎች በሰብዓዊ መብት ረገድ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የሚሠራው ሥራ ጥሩ ቢሆንም፤ ለሌሎች አካላትም ተደራሽ ለማድረግ የኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት አስተምህሮ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ወይዘሮ እፀገነት አስገንዝበዋል፡፡

አክለውም፤ ክፍተት በሚታይባቸውን የሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን በማስተባበር፣ የክትትል እና የምርምር ሥራውን በትኩረት እንዲሠራም አሳስበዋል፡፡ ብዙ የሕዝብ ቁጥር ባለባቸው አካባቢዎች በጥናት ተመሥርቶ ተጨማሪ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን መክፈት እንደሚያስፈልግም ሰብሳቢዋ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በሥርዓተ-ትምህርቱ ተካትቶ እንዲሰጥ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ስምምነት መፈጸሙን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም፤ ከሌሎች አካላት በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የመጡ ጥቆማዎችን እንደግብዓት በመውሰድ እና በማጥናት፣ ኮሚሽኑ በየጊዜው መግለጫ ስለሚሰጥ፣ ለሕዝቡ ትክክለኛውን መረጃ እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለመሆን ኮሚሽኑ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ የኮሚሽኑ ዓቅም ውስን በመሆኑ ትኩረት በሚደረግባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች በመድረስ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በቀጣይም ለሕዝቡ የበለጠ ተደራሽ ለመሆን፤ በክልል ዋና ከተሞች ካሉት ስምንት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በተጨማሪ፣ ሌሎች ተጨማሪ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን መክፈት አስፈላጊ እንደሆነም ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ክብርት ወይዘሮ ራኬብ መሰለም፤ የዓለም-አቀፍ መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ፣ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋም ለመፍጠር እንዲሁም በቅንጅት ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ የሚታሠሩ ሰዎች መኖራቸውን እና የተጠረጠሩ ሰዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ረጅም ጊዜ የሚታሠሩበት ሁኔታ እንዳለም፤ ክብርት ወይዘሮ ራኬብ ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡

ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም የዜጎች መፈናቀል እንዲቆም መሠራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ተፈናቃዮች በ2013 ዓ.ም. በተደረገው ሀገር-አቀፍ ምርጫ እንዲሳተፉ መደረጉንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡