(ዜና ፓርላማ)፤ የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አንደኛው የፓርላማ የምርምር ኮንፈረንስ ‹‹ፓርላማ፣ ዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብቶች›› በሚል ርዕስ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የስብሰባ ማዕከል(ECA) በመካሄድ ላይ ነው፡፡

ኮንፈረንሱን በንግግር የከፈቱት የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በመክፈቻ ንግግራቸውም በዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ምክር ቤቶች የዴሞክራሲ ስርዓት መገንቢያ መድረክና መሳሪያ ሆነው እንደሚያገለግሉ ገልፀዋል፡፡

በዚህ ዘመን በተለይ እያደጉ ባሉና በሽግግር ላይ ባሉ ሀገራት  ምክር ቤቶች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከጥናትና ምርምር ተቋማት፣ ከሙያ ማህበራት፣ ከሲቪል ማህበረሰቡ ጋር የሚያደርጉት የሰመረ ግንኙነት የሀገራቱን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በመፍታትና ሀገራቱን በማሳደግ በኩል አይነተኛ ሚና እንደሚጫወትም አብራርተዋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ የማደግ እምቅ አቅም እና ተስፋ ያላት ናት ያሉት አፈ-ጉባኤው ይህን አቅም ወደ ተግባር ለመቀየርና ተስፋችንን እውን ለማድረግ ደግሞ ጥናትና ምርምር ወሳኝ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

አክለውም የምክር ቤት አባላት ህዝብን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለው ባመኑባቸው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ይከራከራሉ፤ ህግ ያወጣሉ፤ መንግሰትን ይቆጣጠራሉ፡፡ በምክር ቤቱ የሚደረጉ ክርክሮች እንዲሁም የሚወጡ ህጎች ደግሞ በጥናት የተለዩ፣ በቂ ማስረጃ ያላቸውና አመክኖአዊ ምክረሃሰብ ላይ የተመሰረቱ ሲሆኑ ተቀባይነት ያላቸውና ለታሰበላቸው ኣላማ ሊውሉ የሚችሉ ውሳኔዎችና ህጎች የማውጣት እድላቸው ይሰፋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሌላ መልኩ ህግ ፈጻሚው በተነጻጻሪነት የተሻለ የመረጃ እና የእውቀት ምንጮች ያሉት በመሆኑ ምክር ቤቶች ህግ አውጪውን በሚቆጣጠሩበት ወቅት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የመረጃ እጥረት መሙላት የሚያስችል አሰራር መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህን በመረዳት የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በህገ መንግሰቱ የተሰጡትን ተልእኮዎች ሲወጣ የሚያከናውናቸው ተግባራት በመረጃ፣ በእውቀት እና በተቀመረ ልምድ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የዛሬው መድረክም የፓርላሜንታዊ የምርምር መረብ መጠናከር ም/ቤቱ እያካሄደ ለሚገኘው የሪፎርም /የለውጥ/ አካሄድ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥና ፓርላማውም በጥናትና ማስረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ በተለይም በሕግ አወጣጥ፤ በክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የውክልና ተግባራትን በተገቢው ሁኔታ ለማገዝ የሚረዳ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ኔትወርኩ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የምርምር ተቋማትን፣ ቲንክ-ታንክ (ሃሳብ አመንጪ ተቋማትን)፣ የሲቪል ማኅበረሰቡንና የሙያ ማህበራትን ችግር ፈቺ የሆኑ የምርመር ተግባራትን በማካሄድ የሚጠበቅባቸውን ለብሄራዊ ልማት አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችሉ ለማስቻል የሚረዳ ነው፡፡

ከዚህ አንጻር ዛሬ ይህ የምርምር መረብ ራሱ ከሚያበረክታቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች ባሻገር  የምክር ቤታችንን የጥናትና ምርምር አቅም በመገንባትም ወሳኝ ሚና እንዲጫወት እንጠብቃለን፡፡ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኮንፈረንሱ የሚቀርቡት የጥናት ጭብጦችም ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተመረጡ በመሆናቸው ለታሰበው አላማ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ የምርምር ኮንፈረንስ በመደበኛነት በየአመቱ የሚከናወኑ ሲሆን ኮንፈረንሱ የሁለት ቀናት ቆይታ የሚኖረው ይሆናል፡፡