"ህጎች ሲወጡ ቅድሚያ ለሀገርና ለሕዝብ የሚያስገኙት ጥቅም በግልጽ ታውቆና ተፈትሾ ሊሆን ይገባል" - የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ -
ዜና ፓርላማ - መጋቢት 03 ቀን፣ 2017 ዓ.ም፤ ሕጎች ሲወጡ ቅድሚያ ለሀገርና ለሕዝብ የሚያስገኙት ጥቅም በግልጽ ታውቆና ተፈትሾ ሊሆን እንደሚገባ የኤፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ አስገንዝበዋል፡፡
አፈ-ጉባኤው ይህንን ያስገነዘቡት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2017 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለአማካሪ እና ለአስተባባሪ ኮሚቴዎች ቀርቦ ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው።
በዚሁ ጊዜ አፈ-ጉባኤው ህጎች ሲወጡ ቅድሚያ ለሀገርና ለህዝብ የሚያስገኙት ጥቅም በግልጽ ታውቆና ተፈትሾ ሊሆን እንደሚገባ ገልፀው፤ ኮሚቴዎች ህግችን የሚመረምሩበት የድርጊት መርሀ-ግብር መቀመጥ እንዳለበት አመላክተዋል።
የቋሚ ኮሚቴዎች ህጎች ከወጡ በኃላ አፈፃፀማቸውን መከታተልና ለህብረተሰቡ ቀጣይነት ባለው መልኩ በተለያየ ዘዴዎች ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባቸው የተከበሩ አፈ ጉባዔ አስገንዝበዋል፡፡
አካታች የሀገራዊ ምክክር በማድረግና የሽግግር ፍትህ ሥርዓቱን በሁሉም አካባቢ በመተግበር የኢትዮጵያን ሠላም ማፀናት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ በ2017 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት ውስጥ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ ጉልህ ተግባራትን እንዳከናወነ የምክር ቤቱ አፈጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ገልፀዋል።
በግማሽ ዓመቱ ምክር ቤቱ በሕግ አወጣጥ፣ በክትትልና ቁጥጥር፣ በፓርላማ ዲፕሎማሲ እና በህዝብ ውክልና ዘርፎች ውጤታማ ስራዎችን እንደከናወነ አስገንዝበዋል።
የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ በግማሽ ዓመት ውስጥ የተሻለ አፈጻፃም ማሳየቱን ገልጸው፤ በክፍተት የታዩትን በቀጣይ ማስተካከያ ለማድረግ ሁለንተናዊ ጥረት የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
ምክር ቤቱ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎቹ ጥሩ አፈፃፀም ያሣዩ ተቋማትን ዕውቅና በመስጠት እና በማበረታታት እንዲሁም በአፈፃፀማቸው ችግር የሚስተዋልባቸውን በማረም ተጠያቄነትን ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል፡፡
የምክር ቤት ጽ/ቤት የሙያዊ አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ንጉሤ መሸሻ (ዶ/ር) የምክር ቤቱን ግማሽ ዓመት አፈፃፀም ባቀረቡበት ወቅት በህግ አወጣጥ ዘርፍ ምክር ቤቱ እንዲያጸድቅ ከቀረቡለት 37 አዋጆች መካከል 27 ህጎችን ያጸደቀ ሲሆን፤ አስሩ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ነው ያብራሩት።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በአስፈፃሚ ተቋማት ባደረጉት የክትትልና ቁጥጥር ስራ ከዕቅድ በላይ ማከናወን እንደተቻለ የገለፁት ዶክተር ንጉሤ፤ ኮሚቴዎቹ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመስክ ምልከታዎች በማድረግ አንገብጋቢ የሆኑ የህዝብ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ለአስፈፃሚ ተቋማት ግብረመልስ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በተመሳሳይም በህዝብ ውክልና ስራ የምክር ቤት አባላት ህዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ሲወያዩ መቆየታቸውንና የተሻለ ግብዓት የተገኘ መሆኑን ያብራሩት ዶክተር ንጉሴ፤ በሌላ በኩል በፓርላማ ዲፕሎማሲ ዘርፍ 15 የወዳጅነት ዲፕሎማሲ ግንኙነቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ የሚወጡ ህጎች ህዝቡን የሚጠቅሙና ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ ሊሆኑ ይገባል፤ እንዲሁም የአዋጆችን ትክክለኛ ትርጉም ህዝቡ እንዲያው ቢደረግ ሲሉ የአማካሪና አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ጠቁመዋል።
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives