"የኦዲት ግኝትን መሰረት በማድረግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል " የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ 

(ዜና ፓርላማ) ሰኔ 17 2017 .ም፤ አዲስ አበባ፤ የኦዲት ግኝትን መሰረት በማድረግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ሲሉ የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለፁ፡፡

ምክር ቤቱ ባካሄደው 39 መደበኛ ስብሰባው፤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የመንግስት መስሪያ ቤቶች 2016 በጀት ዓመት የሂሳብ የፋይናሽያል ህጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን ገምግሟል፡፡

በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት መሰረት፤ የኦዲት ግኝት ክፍተት ባሳዩ ተቋማት ላይ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ምክር ቤቱ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ የተከበሩ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አመላክተዋል፡፡

የመንግስት ወጪ፤ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የህግ እና ፍትሕ ጉዳዮች  ቋሚ ኮሚቴ አቅደው አሰፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ  የኦዲት ግኝቶች ክፍተቶችን ለማረም በትኩረት እንዲሰሩ ሲሉ የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ  አስገንዝበዋል፡፡

ፍትህ ሚኒስቴር እና ገንዘብ ሚኒስቴር በጋራ በመሆኑ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የመንግስት እና የህዝብ ሃብት በአግባቡ እንዲመሩ ማድረግ እንዳለባቸው አፈ-ጉባኤው አሳስበዋል፡፡

የመንግስት ወጪ፤ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ የሽመቤት ደምሴ (/) በበኩላቸው፤ የባለበጀት መስሪያ ቤቶች የኦዲት ግኝት ክፍተቶችን ለማረም እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የተቋማትን የማስፈጸም አቅም በማሳደግ የኦዲት ክፍተቶችን ለማረም በትኩረት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡