null “Ethiopian pulp and paper factory is in the state of loss”, the standing committee noted.

ኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት ማምረቻ አክሲዮን ማህበር በነጻ ገበያ ተወዳዳሪ በመሆን መንግስትን በኢኮኖሚው ለመደገፍ ታስቦ የተቋቋመ ቢሆንም የታለመለትን ግብ እያሳካ ካለመሆኑም ባሻገር በኪሳራ ላይ እንደሚገኝ በኢፈዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳወቀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የአክሲዮኑን የ2010 በጀት ዓመት የ9 ወራት የዕቅድ አፈጻፀም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

ተቋሙ ከተቋቋመ ረጅም አመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ዓላማውን ከማሳካት አንጻር ክንውኑ በወረቀት ማምረት ማደራጀት እና የካርቶን ማምረቻ ምርት አጠቃላይ ሂደት 40.6% እና ከሽያጭ 38.95% ብቻ መሆኑን፣ ይህንን ተከትሎም በበጀት ዓመቱ ከ3.8 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ውስጥ መግባቱን፣ ሆኖም ከአምናው ጋር ሲነጻፀር የኪሳራ መጠኑ መቀነሱን የተቋሙ አመራሮች ገልጸዋል፡፡

ለድርጅቱ አፈጻፀም ዝቅተኛነትም የጥሬ ዕቃ፣ የኬሚካል፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እንዲሁም የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍልሰት ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ሀላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

ባጋጠሙ ችግሮች ድርጅቱ የማምረት ሂደቱ በተቋረጠ ቁጥር የኪሳራ መጠኑም በሰዓታት እና ቀናት ልዩነት እየጨመረ እንደሚሄድ ተጠቁሟል።

ድርጅቱ በሃገሪቱ ብቸኛ የወረቀትና ፐልፕ ማምረቻ ቢሆንም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከመንግስት በኩል የተደረገው ድጋፍ በጣም አናሳ መሆኑ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም እያሳጣ እንደሆነም ሃላፊዎቹ አክለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ድርጅቱ በተፈጠረው ነጻ ገበያ ተጠቅሞ ተወዳዳሪ ሆኖ አሁን ላይ ከሚገኝበትን ኪሳራ ለመውጣትና በኢኮኖሚው የመንግስትን አቅም ለመደገፍ የሰው ሃይል ብቃት ከማሳደግ፣ ከማቆየት፣ ከማብቃት፣ አማራጭ የኃይል ምንጭና ግብዓትን ከመጠቀም አንጻር ክፍተት እንዳለበት እንዲሁም ድርጅቱ ነባርና ልምድ ያለው ቢሆንም ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ እያመረተ አለመሆኑን ገምግሟል፡፡

የሀገር ውስጥ የወረቀት ፍላጎት ወደ 24% ቢያድግም ድርጅርቱ በዓመት 4% በመቶ ብቻ የምርት አገልግሎት መስጠቱ የወረቀት ፍላጎትን ማርካት አለመቻሉን፣ ይህም መንግስትን በዓመት 6 ቢሎዮን ብር ገዳማ እንዲያጣ ከማድረጉም ባሻገር በሃገር ውስጥ መታተም የሚችሉ የህትመት ስራዎችን በውጭ ሃገራት እንዲታተሙ በማድረግ ለተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እየዳረገው መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል፡፡

በመጨረሻም ድርጅቱ ከሌሎች ማምረቻ ድርጅቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት በማሳደግ ከተለያዩ ፋብሪካዎች የሚገኙ ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም በስፋትና በተደራጀ መልኩ ጥናት በማድረግ ለቀጣይ በማቀድ መስራት እንደሚጠበቅበት እና የውስጥ ችግሮቹን በመፍታት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ሀገሪቱን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡