null “House undergoes dynamism in critical approaches”

የምክር ቤቱ የመከታተል ዓቅም በቀጣይነት እየጎለበተ መምጣቱ ተመላከተ

የካቲት 13፣ 2012 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕግ በተሰጠው ስልጣን መሠረት ሀገራዊ ጉዳዮችን የመቆጣጠር እና የመከታተል ዓቅሙ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መምጣቱ ተመላከተ፡፡

ይህ የተመላከተው፤ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ክቡር ታገሰ ጫፎ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በጽሕፈት ቤታቸው በአካሄዱት ልዩ ቃለ-ምልልስ ነው፡፡ ክቡር አፈ-ጉባዔው በዚህን ወቅት እንዳሉት፤ አስፈጻሚ አካላትን ከመከታተል እና ከመቆጣጠር አንጻር የህዝብ ተወካዮች ክንዋኔ የሚታዩ ለውጥዎችን አስመዝግቧል፡፡

ከዚህም አኳያ በቅርቡ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጋር በተካሄደው የ5ኛው ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 1ኛ ልዩ ጉባዔ ወቅት፤ የምክር ቤቱ አባላት በወከሏቸው እና በሕዝቡ ዘንድ በአጠቃላይ አሉ የተባሉ ጠንካራ ጥያቄዎችን በግልጽነት ማቅረባቸውንም ክቡር አፈ-ጉባዔው ለአብነት አስታውሰዋል፡፡

“በአምስተኛ የሥራ ዘመን የግማሽ ዓመት ክንዋኔ፤ ምክር ቤቱ በ1 መቶ 75 ያህል አስፈጻሚ ተቋማት ክትትል እና ቁጥጥር በማካሄድ ግብረ-መልስ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱ በሰጠው ጠንካራ ግብረ-መልስ የተነሳም የሁለት አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች በሚመለከተው አካል ርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ምክር ቤቱ አስፈጻሚውን አካል በጥንቃቄ እየተቆጣጠረው ይገኛል፡፡

“ምክር ቤት ከነስሙ ምክር ቤት ነው፡፡ ሀገርን እና ሕዝብን የሚጠቅሙ ጉዳዮች ሊመከሩበት ይገባል፡፡ ይህም በሕገ-መንግስቱ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሕገ-መንግስቱ፣ ለሕዝብ እና ለሕሊናቸው ብቻ የሚገዙበት መንስዔ መሆኑን አምናለሁ” ብለዋል ክቡር አፈ-ጉባዔው፡፡

አያይዘው እንደገለጹትም፤ ምክር ቤቱ በግማሽ የሥራ ዘመኑ ብቻ 25 አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 13ቱ የሕግ የበላይነት ተከብሮ እንዲቀጥል የሚያግዙ ሲሆን፤ የተቀሩት 12ቱ ደግሞ የብድር እና የስምምነት አዋጆች መሆናቸውንም ክቡርነታቸው አብራርተዋል፡፡

በምክር ቤቱ ሕገ-ደንብ መሠረት የተያዘው ወር የዕረፍት ጊዜ ቢሆንም፤ የሕዝብ ተወካዮች ወደየመጡበት ስፍራ በመመለስ በዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች ከመላው ሕብረተሰብ ጋር እየተወያዩ መሆናቸውን የጠቆሙት ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ፤ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ዜጎች ምጣኔ-ሀብታዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ትኩረት እንደተሰጠ አክለው አስገንዝበዋል፡፡

በተጠናቀቀው ግማሽ የሥራ ዘመን በፌዴራል ደረጃ እና በክልሎች በአባላት አማካይነት በአካል የተደረጉት የመስክ ምልከታዎች፤ የክትትል እና ቁጥጥሩ ሥራ ዐበይት ተግባራት እንደነበሩ አፈ-ጉባዔው አስታውሰዋል፡፡ ከዚህም አንጻር በታላቁ የኀዳሴ ግድብ የተደረገው ጉብኝት በምሳሌነት የሚነሳ ሲሆን፤ ምክር ቤቱ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመለገስ ከዓባይ ወንዝ የታችኛዎቹ ተፋሰስ ሀገራት ጋር የሚካሄዱት ድርድሮች የሀገርን ጥቅም ለድርድር የማያቀርቡ መሆናቸውንም በቅርበት እንደሚከታተል አስታውቀዋል - አፈ-ጉባዔው፡፡

በተጨማሪም ዘንድሮ እንዲካሄድ ቀን የተቆረጠለት ሀገራዊ ምርጫ ጉዳዮች፣ የሀገር ሰላም እና ደኀንነት እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ጉዳዮች የምክር ቤቱ ዐበይት ሥራዎች ሆነው መዝለቃቸውንም ክቡር ታገሰ አመልክተዋል፡፡

ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አንጻርም ለምክር ቤቱ የሚቀርቡትን የኦዲት ሪፖርቶች በመንተራስ ሰፋፊ ሥራዎች መሠራታቸውን የገለጹት ክቡር አፈ-ጉባዔው፤ በርሳቸው ሰብሳቢነት የሚመራ ልዩ የኦዲት ጉዳዮች ኮሚቴ ተዋቅሮ ብልሽቶች እንዲስተካከሉ እና የሀብት አስተዳደሩ ሥርዓት እንዲዘምን እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

አሥራት አዲሱ

   የምክር ቤቱ ፀሐፊ