null “NDRMC is subject to audit findings”

የፋይናንስና ግዥ አሰራርን ተከትሎ አለመስራትና ሃላፊነትን በተገቢው አለመወጣት የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንን ለኦዲት ግኝት እያጋለጠ ነው ተባለ፡፡

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንን የ2012 በጀት ዓመት በተመለከተ የሂሳብ ኦዲትን ገምግሟል፡፡

በግምገማው ወቅትም ቋሚ ኮሚቴው በኮሚሽኑ በተከናወነ ሂሳብ ኦዲት ግኝቶችን አስመልክቶ ባዘጋጀው ጥያቄ መሰረት የተጀመረው ውይይት ኮሚሽኑ በራሱ በተፈጸመው ስንዴ፣ አልሚ ምግብ፣ የመኪና ወንበርና ተጓዳኝ ልብስ በድምሩ በ1.9 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ግዥ የተፈጸመ ሆኖ ሳለ የገቢ ደረሰኝ አለመቅረቡ በግኝቱ የተረጋገጠና ለምንስ ተከታትሎ ለማቅረብ አልተቻለም ሲል ጠይቋል፡፡

ዋና ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ኦሪጅናል የገቢ ደረሰኞች በመጋዘኖች እንደሚገኝና ኮሚሽኑ የክትትልና የቁጥጥር ስራ እንደሚሰራ ነው በምላሻቸው ያስቀመጡት፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ኮሚሽኑ በስሩ ካሉ ቅርንጫፍና ከተጠሪ ተቋማት ያሉ መረጃዎችን ለማቅረብ ያለመቻል በስራው ላይ ክፍተት እየፈጠረ እንደሆነ ኮሚሽኑ ቆጥሮ የወሰደውን ሃላፊነት በተገቢው እየተወጣ ካለመሆኑም በተጨማሪ መንግስታዊ ባልሆኑት የውጭ ድርጅቶችም ግዢ ተፈጽመው ለእርዳታ በመጡ እህሎችና አልሚ ምግቦች ላይም ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ለኮሚሽኑ በድምሩ 1.3 ቢሊዮን ብር የቀረጥ ሂሳብ ወጪ ተደርጎ የገቢ ደረሰኝ በዝርዝር ያለመቅረቡ ኦዲት ግኝት ያሳያል ብሏል፡፡

ኮሚሽኑ የፌዴራል የግዥ መመሪያን ባልተከተለ በተለያዩ ቀናት የመኪና ጎማ፣ የፕላስቲክ ሽት፣ የምግብ ዘይት እና ወተት ባጠቃላይ 544 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም 556 ሚሊዮን ብር በላይ በጨረታ መግዛት ሲገባ በቀጥታና ከአንድ ድርጅት ግዥ መፈጸሙን ተገምግሟል፡፡

ኮሚሽነሩ አቶ ካሳ ኮሚሽኑ በሰውና በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱት አስቸኳይ ድጋፍ የሚያደርግ ቢሆንም አሁን ላይ ምቹ ያልሆኑ የፋይናንስ አሰራሮችም እንዳሉ ቢነገርም ከግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመጡ አመራሮችም በበኩላቸው በኮሚሽኑ የተለያዩ የግዥ አማራጭ አሰራሮች እያሉ ስርዓትን ያልተከተለ የግዥ ሂደትን መከተል እንደመረጠ አንስተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ኮሚሽኑ ሰራተኞች የተከፈለውን ውሎ አበል ሳያወራርድ በውዝፍ የተያዘ ከ608 ሚሊዮን ብር በላይ የተያዘ እና ለጉልበት ሰራተኞች ክፍያ፣ ለመጋዘን ኪራይ እንዲሁም ዝናብ ዕጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ድርቅን ለመቋቋም ተብሎ ለክልሎች የተሰራጨ 806 ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ የሚደርስ ብር የወጪ ማስረጃ ያልቀረበ መሆኑ በድክመት አንስቷል፡፡

ኮሚሽነሩ በበኩላቸው ክልሎች ባቀረቡት የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ የተወራረደና የወጪ ማስረጃ በክልሎች እጅ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ሃላፊነት የወሰዳቸውን የመንግስት ሃብት ለታለመለት ዓላማ መዋል አለመዋሉ የሚረጋገጥበት የመንግስት ስርዓት እንዳልተገበረ የሚያሳይና ተጠያቂነት ያለበት ስለሆነ በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት በትኩረት መታሰብ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡       

ቋሚ ኮሚቴው አሁን ላይ እየገቡ ያሉት የኢንዱስትሪ ግብዓት የሆኑ ቫይታሚንና ሚኒራሎች በኮሚሽኑ የበላይ አመራር ውሳኔ መሆን ሲገባው ያለ ህጋዊ ውክልና በሎጀስቲክስ ዳይሬክቶሬት በተጻፈው የውስጥ ደብዳቤና ያለ ውል ስምምነት ግዥ መፈጸሙ አግባብነት እንደሌለውም ገምግሟል፡፡

በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ኮሚሽኑ በዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝት ሆነው ከተነሱ ሃያ እንድ ነጥቦች 3ቱን ላይ ብቻ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱ ከበቂ በታች እንደሆነና ችግሮችን በትኩረት በማየት አሁን ካለበት ኦዲት ግኝት ለመውጣት መስራት እንዳለበት አሳስቧል፡፡    

ዘጋቢ:- እያሱ ማትዮስ