null Board urges public donate blood, save lives

ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ደም በመለገስ የወገኑን ህይወት መታደግ እንደሚገባው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃጸም መርማሪ ቦርድ አባላት ጥሪ አቀረቡ፡፡

ሚያዚያ 15 ቀን 2012 ዓ.ም በአገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሲባል የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃጸም መርማሪ ቦርድ በጤና ሚንስቴር በመገኘት ደም ለግሷል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበት ለወላድ እናቶች፣ ለህፃናትና በተለያዩ አደጋዎችና በሽታዎች ደም የሚያስፈልጋቸው በርካታ ወገኖች በመኖራቸው የቦርዱ አባላት በፍቃደኝት ደም ለመለገስ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡

የቦርዱ ፀሀፊ የተከበሩ ወ/ሮ ፋንታዬ ወንድም በበኩላቸው ደም መለገስ የሌሎችን ህይወት የሚታደግና የህሊና እርካታን የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአለምና በአገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ ደም የመለገስ ተግባሩ እየተቀዛቀዘ በመሆኑ ህብረተሰቡ ይህን ተረድቶ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ደም በመለገስ የወገኑን ህይወት መታደግ እንደሚገባውም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ 

የጤና ሚንስቴር ሚንስትር ክብርት ወ/ሮ ሰሀርላ አብዱላሂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃጸም መርማሪ ቦርድ አባላት በጤና ሚንስቴር በመገኘት ያካሄዱት የደም ልገሳ    የሚመሰገንና ሌሎች አካላትን የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የቦርዱ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል መንግስት እና ህብረተሰቡ በርካታ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ የቦርዱ አባላትም የተሰጣቸውን ተልዕኮ ከማከናወን ጎን ለጎን ደም በመለገስ ለወገን ያላቸውን አለኝታነት መግለፅ በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ህብረተሰቡ በመንግስትና በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን የጥንቃቄ መልዕክቶችን ሊተገብር እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

ዘጋቢ፡- ኃ/ሚካኤል አረጋኸኝ