null Board urges zones persistently fight Corona virus spread

የሀላባ እና ከምባታ ጠንባሮ ዞኖች የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እያከናወኑ ያሉት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ

ፓርላማ፤ ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ በሀላባ እና በከምባታ ጠምባሮ ዞኖች የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻፀምን አስመልክቶ በዞኖቹ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ከተቋቋሙ ግብረ-ኃይሎች ጋር ተወያይቷል፡፡

ቦርዱ በሁለቱም ዞኖች ኮቪድ-19ን ለመከላከል ግብረ ሃይሎች ተቋቁመውና ዕቅድ አዘጋጅተው ወደ ተግባር መግባታቸውን፣ የሀብት ማሰባሰብ ስራዎች መካሄዳቸውን፣ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨመጫ መሰጠቱን፣ በመናኽሪያና በዋና ዋና መግቢያ በሮች ላይ የሙቀት ልኬት እንዲኖር መደረጉን፣ በዞኖች በሚገኙ ወረዳዎች የለይቶ ማቆያዎችና የህክምና መስጫ ማዕከሎች መዘጋጀታቸውን ተመልክቷል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ጠንካራ የቤት ለቤት ቅኝትና አሰሳ መደረጉን፣ ሁለቱም ዞኖች ከውጪ አገር የመጡና በቫይረሱ የተያዙ ግለሰቦችን ጠንካራ ክትትል በማድረግ መያዛቸውና ወደ ማቆያ ማስገባት መቻላቸውን በጠንካራ አፈጻፀም አስቀምጠዋል፡፡

እነዚህ ሰዎች አምልጠው ወደ ህብረተሰቡ ቢገቡ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ሊከሰት እንደሚችል አመላክተው በቀጣይም ይህን መሰል ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ነው ያሉት፡፡

አያይዘውም ሀብትን በማሰባሰብ ረገድ ጠንካራ ስራዎች መሰራታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ፍትሃዊ ክፍፍልና ስርጭት ሊኖር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ቦርዱ በሁለቱም ዞኖች በትራንስፖርት አጠቃቀም ረገድ አሁንም በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቸልተኝነት እንዳለ በመኪኖች ላይ ሾፌሮችም ሆኑ መንገደኞች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ያለማድረግጋቸውንና በአንድ ሞተር ሳይክል ከሁለት ሰው በላይ ተጭኖ የሚንቀሳቀስ መሆኑን የቦርዱ አባላት በውስንነት አንስተዋል፡፡

በቀጣይም ብዙ ቁጥር ያላቸው የዞኖቹና አካባቢዎች ተወላጆች ከደቡብ አፍሪካ የሚመጡ በመሆኑ በአግባቡ ተከታትሎ ወደ ማቆያ ከገቡ በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ማድረግ እና ከአጎራባች ዞኖች ጋር በቅንጅት መስራቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃ/ሚካኤል አረጋኸኝ