null Comitee of the House advised Dire Dawa Industrial park should immediately on the truk of work.

የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተመርቆ በአስቸኳይ ወደ ስራ መግባት እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና እንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቡድን   የድሬዳዋን ኢንዱሰትሪ ፓርክ፣ እንዲሁም በከተማዋ ስር የሚገኙትን የኢንዱስትሪ መንደሮች፣ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ዘርፉን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ጉብኝት አድርጓል፡፡

በ150 ሄክታር ላይ ያረፈው እና 15 ሼዶች ያሉት የድሬዳዋ ኢንድስትሪ ፓርክ ሙሉ ግንባታው ተጠናቆ በቅርብ ጊዜ ተመርቆ ስራ የሚጀምር መሆኑን ቡድኑ ባደረገው የመስክ ምልከታ አረጋግጧል፡፡

ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከተመረቀ በኋላ በአልባሳት ማምረት ዘርፍ ለሚሰማሩ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ኢንቨስተሮች የሚተላለፍ ሲሆን ከ10ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተመሳሳይም ቡድኑ በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር ማምረቻና መሸጫ ቦታዎችን በጎበኘበት ወቅት የማምረቻ ቦታዎች የዲዛይን ማሻሻያ ስራ በበጀት እጥረት ምክንያት ግንባታው መጓተቱን ያረጋገጠ ሲሆን በአንጻሩ ከሰባቱ  የመሸጫ ቦታዎች አምስቱ  ግንባታቸው ተጠናቆ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምሩ መረዳት ችሏል፡፡       

በሌላ በኩል በኢንቨስትመንት ስም ለዘመናት በርካታ መሬት አጥረው በተቀመጡ ባለሃብቶች ላይ ከተማ አስተዳደሩ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነም ቡድኑ አረጋግጧል፡፡

የንግዱን ዘርፍ ፍትአዊ ከማድረግ አንጻር ከተማ አስተዳደሩ ዘርፈብዙ ስራዎችን ያከናወነ ቢሆንም መንግስት በድጎማ በሚያስገባቸው በነዳጅ ፣በዘይትና በስንዴ ዱቄት ስርጭት ዙሪያ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ነው ቡድኑ የታዘበው፡፡

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እንዲሁም የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር በበኩላቸው በንግዱ ዘርፍ በርካታ ችግርች እንዳሉ ገልጸው ህገወጥ ንግድን ህጋዊ ለማድረግ ፣ የነዳጅ አቅርቦት፣ የዘይትና የስኳር ስርጭት የመልካም አስተዳደር ችግር መንስዔ እንዳይሆኑ በትኩረት እየሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የበጅት እጥረትን ጨምሮ የሚስተዋሉ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የገለጹት አቶ አብዲ በኢንቨስትመንት ስም ታጥረው የተቀመጡ መሬቶችን የማስመለስ ሂደቱ ውጤት የታየበት እንደሆነና በቀጣይም የተሻለ ስራ ለማከናወን ቅንጅታዊ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስገነዘቡት፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባልና የንግድ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ዘውዱ ከበደ በበኩላቸው በሰጡት ግብረ መልስ ህገወጥ ንግድን ህጋአዊ ለማድረግ፣ የንግድ ፈቃድ አሰጣጡን ለማዘመን፣ እምዲሁም በየተቋማቱ ያሉትን ችግሮች ለመለየት የተደረገውን ጥረት በጥንካራ ጎን አንስተዋል፡፡

በአንጻሩ በተቋማት የአሰራር ተግዳሮት ናቸው ተብለው የተለዩ ችግሮችን አቅዶ ከመፍታት አንጻር ውስንነቶች እንዳሉ እና በቅርብ ጊዜ ወደ አመራርነት የመጡ ግለሰቦች አዲስ ነኝ በማለት ከኃላፊነት የመሸሽ አዝማሚያ የሚታይባቸው መሆኑን አቶ ዘውዱ በክፍተት አመላክተዋል፡፡

በንግዱም ሆነ በኢቨስትመንቱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮች በህዝብ ዘንድ ቁጣ ከመቀስቀሳቸው በፊት ደረጃ በደረጃ መቀረፍ እንዳለባቸው እና ከቅርብ አመታት ወዲህ በከተማዋ የሚስተዋሉ የተዝረከረኩ አሰራሮችን ለይቶ ለማስተካከል ሁለንተናዊ ርብርብ ሊደረግ ይገባል ሲሉ አቶ ዘውዱ አሳስበዋል፡፡