null Committee discusses arms ownership and utilization with commissioners

ቋሚ ኮሚቴው በጦር መሳሪያ  አያያዝና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ  ዙሪያ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን ጨምሮ ከክልልና ከተማ አስተዳደር ፖሊስ  ኮሚሽነሮች  ጋር ተወያዬ

ታህሳስ 8 ፣ 2012 ዓም. ፤ በኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጦር መሳሪያ አያያዝና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን ጨምሮ  ከክልልና ከተማ አስተዳደር ኮሚሽነሮችና ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል ፡፡

ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የሃገራችን ብሎም የዜጎቻችን የእለት ተዕለት ደህንነት ስጋት ውስጥ እየጣለ እንደሚገኝ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ አብራርተዋል ፡፡

የሕዝባችን ደህንነት ለማስጠበቅና ህገ-ወጥ የሆነውን የጦር መሳሪያ ዝውወውር ለመቆጣጠር  እንዲሁም  ስርዓት ባለው መልኩ ለማስተዳደር የረቂቅ አዋጁ  ተቀዳሚ ዓላማ እንደሆነ አቶ ተስፋዬ ጠቅሰዋል ፡፡  

ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በሃገራችን ሸቀጥ በሚመስል መልኩ እየተዘዋወረ በኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች እጅ ላይ መውደቁ  ሃገራችን የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ወደ ኋላ የሚገታ መሆኑ ስለታመነበት ረቂቅ አዋጁ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑንም ሰብሳቢው አክለዋል ፡፡

በህገ -ወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር ምክንያት የሚሰራው ወንጀል እየተበራከተ መምጣቱ በሃገርም ሆነ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ስጋት ስለፈጠረ ረቂቅ  አዋጁ የማይተካ ሚና እንዳለው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው ገልጸዋል ፡፡

ለህገ-ወጥ መሳሪያ ዝውውር መበራከት የቅጣት መቅለል ፣  ህገ- ወጡን መሳሪያ ይዞ የተገኘ ተሸከርካሪ ላይ ጠንከር ያለ ርምጃ አለመወሰዱ ለዝውውሩ መበራከት በምክንያትነት ከተጠቀሱት መካከል ይገኙበታል ፡፡

የጦር መሳሪያ አያያዝና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጁ ከአርሶ አደሩ ፣ ከከፊል አርብቶና አርሶ አደሩ እንዲሁም ከአርብቶ አደሩ የሕብረተሰብ ክፍል  ጋር ተስማሚ በሆነ መልኩ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አቶ ተስፋዬ ጠቅሰዋል ፡፡

በረቂቅ አዋጁ መሻሻል ፣ መጨመርና መቀነስ ያለባቸው ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን ፣ በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች ሃሳቦች እየዳበሩ በተለይም ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን የሚገታ አዋጂ እንደሚጸድቅ አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል ፡፡