null Committee of the House urged that the Ethiopian Pharmaceutical Supply Agency (EPA) has needed to address the problem of supply and distribution of medicine and medical equipment.

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጄንሲ በመድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦትና ስርጭት ላይ የሚታየውን ችግር ፈጥኖ ሊፈታ ይገባል ሲል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፣

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጄንሲን የ2011 በጀት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

የአገር ወስጥ መድሃኒት አምራቾችን አቅም ከማሳደግ አንፃር፣ ከሚመለከታቸው ባለድሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ከመስራት፣ የዱቤ ሽያጭ ሂሳብን ከመሰብሰብና ጊዜ ያለፈባቸውን መድሃኒቶችና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ከማስወገድ አኳያ ኤጄንሲው ምን ሰራ የሚሉት በቋሚ ኮሚቴው ከተነሱት ጥያቄዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሎኮ አብርሃም ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት የአገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾችን አቅም በማጠናከር የህክምና መገልገያዎችንና መድሃኒቶችን እንዲያቀርቡ ለማስቻል ቢታቀድም ዋናው ችግራቸው የውጪ ምንዛሪ እጥረት በመሆኑ በኤጄንሲ አቅም ብቻ ሊፈታ አለመቻሉንና መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የመድሃኒት አቅርቦት ስራን ውጤታማ ማድረግ የሚቻለው የግዥ ስርዓቱን በማሻሻል እንደሆነ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ተግባሩ በርካታ ተዋናዮች ያሉበት በመሆኑና ሁሉም ተቀናጅተው ባለመስራታቸው በመድሃኒቶቹ አቅርቦትም ይሁን በአቀማመጣቸው ላይ ችግሮች ይስተዋላሉ ብለዋል፡፡

ጤና ተቋማት ላይ የሚታየው የመድሃኒት አቅርቦት ችግር የሚጀምረው ከትንብያ መረጃ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ተቋማቱ የሚሰጡት መረጃ ኃላፊነት የጎደለውና ተቀራራቢ ባለመሆኑ የሚፈጠር ክፍተት ስለሚሆን የጤና ተቋማቱ የአቅርቦት ኃላፊነቱን እንዲወስዱ መደረግ አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

መድሃኒት ወደ ጤና ተቋማቱ ከገባ በኋላ በህገ-ወጥ መንግድ ወደ ገበያ የሚወጣበት ሁኔታ ስለሚኖር አለም ላይ ካሉ ተመሳሳይ ተቋማት ተሞክሮዎችን በመውሰድ የቁጥጥርና የመረጃ ቅብብሎሽ ስርዓቱን ማዘመን ይገባል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የዱቤ ሽያጭ ተሰብሳቢ ሂሳብን በተመለከተ ከተወሰኑ ተቋማት በስተቀር የአብዛኛዎችን ሰብስበናል ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በሰጠው ማጠቃላያ አስተያየት እንዳለው የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጄንሲ አሰራሩን ለማዘመንና የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ እንዲሁም በየቅርንጫፎቹ አዳዲስ መጋዘኖችን በመገንባት የመጋዘን ኪራይን ለማስቀረት የሚያደርገውን ጥረት በጥንካሬ አንስቷል፡፡

 

ኤጄንሲው በመድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦትና አቀማመጥ ላይ ያሉትን ከፍተኛ ችግሮችና ቅሬታዎች ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ያሳሰበው ቋሚ ኮሚቴው የትንብያ መረጃዎች የተቀራረቡ እንዲሆኑና አሰራሩ ለህገ-ወጦች በር የሚከፍት አንዳይሆን ከባለድርሻ አካለት ጋር ተቀራርቦ መስራት ይገባል ብሏል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አክሎም ኤጄንሲው በቀጣይ የአገር ውስጥ አምራቾችን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከቦርድ አመራሩ ጋር በመመካከር በመፍታትና አቅማቸውን በማሳደግ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን እንዲፈቱ ማስቻል ይጠበቅበታል ሲል አሳስቧል፡፡