null Committee of the House visited Kalliti revenue secretariat.

የገቢዎች፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቃሊቲ ጉምሩክ ጽ/ቤት ባደረገው የመስክ ምልከታ አገልግሎቱን ከኪራይ ሰብሳቢነት እና ከብልሹ አሰራር የጸዳ ለማድረግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን አስመልክቶ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ጋር በነበረው ቆይታ መጋዘኖች አከባቢ የተተው እና የተወረሱ ንብረቶች አያያዝ ፣አደረጃጀት እና አወጋገድ ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል፡፡

የተተው እና የተወረሱ ንብረቶች በባህሪያቸው ተለይተው መቀመጣቸው በጥንካሬ የሚታዩ ቢሆንም ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎችን ከማስወገድ እና ወደ ገቢ ከመቀየር አንጻር እንዲሁም ለጤና ጠንቅ የሆኑ ኬሚካሎችን ለይቶ ከማስቀመጥ ረገድ ክፍተቶች እንዳሉ ቋሚ ኮሚቴው መመልከት ችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ለአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን በመፈተሸ በቀጣይ የሚሰጡትን አገልግሎቶች ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከብልሹ አሰራር የጸዳ ለማድረግ ተቋሙ ያሉበትን የአሰራር ማንዋል ክፍተቶች በመለየት ለሚመለከተው አካል ማሳወቁን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ተመልክቶታል፡፡

የጉምሩክ የመረጃ ስርአትን ከማዘመን አኳያ የኢትዮጵያን ከስተምስ ማኔጅመንት ሲስተምን በማበልጸግ የሚሰጠው አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢ እና ፍትሃዊ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ወደ ስራ መገባቱን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ያየው ቢሆንም በቀጣይ ወደ ተሟላ ውጤታማነት ለመቀየር በአገልግሎቱ ሰጪውም ሆነ በተጠቃሚው መካከል ያሉ የክህሎት ክፍተቶችን በመሙላቱ ረገድ ተቋሙ ሰፊ ስራ እንደሚጠብቀው አስገንዝበዋል፡፡

በተቋሙ የገቢ እቅድ አፈጻጸም በ8 ወራት 16 ቢሊየን የተሰበሰበ ቢሆንም ከአመቱ አንጻር ሲታይ 19.4 ቢሊየን ያልተሰበሰበ ገቢ እንዳለ በመጠቆም ያሉ የገቢ አማራጮችን በመለየት በአገልግሎት ሰጪውም ሆነ በተገልጋዩ ዘንድ ሃገራዊ ስሜት በመፍጠር ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ህጎች ፣ደንቦችና የአሰራር ማንዋሎችን መሰረት ያደረጉ አሰራሮችን በመዘርጋት የሃገር ስጋት የሆነውን ኮንትሮባንድ ከመከላከልም ረገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጂት በመስራት ተቋሙ በበጀት አመቱ የተጣለበትን ግብ ማሳካት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡